፲፫
፩ ወደ እናንተ ስመጣ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ ሁሉ ነገር በሁለትና በሦስት ምስክር አፍ ይጸናል። ፪-፬ በድካም ተሰቅሎአልና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኃይል በሕይወት ይኖራል። እኛ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንደክማለንና፥ ነገር ግን ስለ እናንተ በሆነ በእግዚአብሔር ኃይል ከእርሱ ጋር በሕይወት እንኖራለን። ፭ በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ፤ ወይስ ምናልባት የማትበቁ ባትሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ እንዳለ ስለ እናንተ አታውቁምን? ፮ እኛ ግን የማንበቃ እንዳይደለን ልታውቁ ተስፋ አደርጋለሁ። ፯ ክፉ ነገርንም ከቶ እንዳታደርጉ ወደ እግዚአብሔር እንጸልያለን፤ እኛ የምንበቃ ሆነን እንገለጥ ዘንድ አይደለም ነገር ግን እኛ ምንም እንደማንበቃ ብንሆን፥ እናንተ መልካሙን ታደርጉ ዘንድ ነው። ፰ ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልምና። ፱ እኛ ስንደክም እናንተም ኃይለኞች ስትሆኑ ደስ ብሎናልና፤ እናንተ ፍጹማን ትሆኑ ዘንድ ለዚህ ደግሞ እንጸልያለን። ፲ ስለዚህ ጌታ ለማፍረስ ያይደለ ለማነጽ እንደ ሰጠኝ ሥልጣን፥ ከእናንተ ጋር ሳለሁ በቁርጥ እንዳልሠራ በሩቅ ሆኜ ይህን እጽፋለሁ። ፲፩ በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ደኅና ሁኑ። ፍጹማን ሁኑ፥ ምክሬን ስሙ፥ በአንድ ልብ ሁኑ፥ በሰላም ኑሩ፥ የፍቅርና የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል። ፲፪ በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። ፲፫ ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ፲፬ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።