፩-፫ ነገር ግን የሚያጸናችሁ ከክፉውም የሚጠብቃችሁ ጌታ የታመነ ነው። ፬ የምናዛችሁንም አሁን እንድታደርጉ ወደ ፊትም ደግሞ እንድታደርጉ ስለ እናንተ በጌታ ታምነናል። ፭ ጌታም ወደ እግዚአብሔር ፍቅር ወደ ክርስቶስም ትዕግሥት ልባችንን ያቅናው። ፮ ወንድሞች ሆይ፥ ከእኛ እንደ ተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለ ሥርዓት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን። ፯ እኛን ልትመስሉ እንዴት እንደሚገባችሁ ራሳችሁ ታውቃላችሁና፤ በእናንተ ዘንድ ያለ ሥርዓት አልሄድንምና፤ ፰ ከእናንተ ዘንድ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት፥ ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት እየሠራን እንኖር ነበር እንጂ፥ ከማንም እንጀራን እንዲያው አልበላንም። ፱ ይህም እኛን ልትመስሉ ራሳችንን እንደ ምሳሌ እንሰጣችሁ ዘንድ ነበር እንጂ፥ ያለ ሥልጣን ስለ ሆንን አይደለም። ፲ ደግሞ ከእናንተ ጋር ሳለን። ሊሠራ የማይወድ አይብላ ብለን አዘናችሁ ነበርና። ፲፩ ሥራ ከቶ ሳይሠሩ፥ በሰው ነገር እየገቡ፥ ያለ ሥርዓት ከእናንተ ዘንድ ስለሚሄዱ ስለ አንዳንዶች ሰምተናልና። ፲፪ እንደነዚህ ያሉትንም በጸጥታ እየሠሩ የገዛ እንጀራቸውን ይበሉ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናዛቸዋለን እንመክራቸውማለን። ፲፫ እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክቱ። ፲፬ በዚህ መልእክት ለተላከ ቃላችን የማይታዘዝ ማንም ቢኖር፥ ይህን ተመልከቱት፥ ያፍርም ዘንድ ከእርሱ ጋር አትተባበሩ። ፲፭ ነገር ግን እንደ ወንድም ገሥጹት እንጂ እንደ ጠላት አትቍጠሩት። ፲፮ የሰላምም ጌታ ራሱ በሁሉ መንገድ ዘወትር ሰላምን ይስጣችሁ። ጌታ ከሁላችሁ ጋር ይሁን። ፲፯ በገዛ እጄ የተጻፈ የእኔ የጳውሎስ ሰላምታ ይህ ነው፤ የመልእክቴ ሁሉ ማስረጃ ይህ ነው፤ እንዲህ እጽፋለሁ። ፲፰ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።