፲፮
፩ ወደ ደርቤንና ወደ ልስጥራንም ደረሰ። እነሆም፥ በዚያ የአንዲት ያመነች አይሁዳዊት ልጅ ጢሞቴዎስ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ፤ አባቱ ግን የግሪክ ሰው ነበረ። ፪ ለእርሱም በልስጥራንና በኢቆንዮን ያሉ ወንድሞች መሰከሩለት። ፫ ጳውሎስ ይህ ከእርሱ ጋር ይወጣ ዘንድ ወደደ፥ በእነዚያም ስፍራዎች ስለ ነበሩ አይሁድ ይዞ ገረዘው፤ አባቱ የግሪክ ሰው እንደ ሆነ ሁሉ ያውቁ ነበርና። ፬ በከተማዎችም ሲዞሩ በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የቈረጡትን ሥርዓት ይጠብቁ ዘንድ ሰጡአቸው። ፭ አብያተ ክርስቲያናትም በሃያማኖት ይበረቱ ነበር፥ በቍጥርም ዕለት ዕለት ይበዙ ነበር። ፮ በእስያም ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አገር አለፉ፤ ፯ በሚስያም አንጻር በደረሱ ጊዜ ወደ ቢታንያ ይሄዱ ዘድን ሞከሩ፥ የኢየሱስ መንፈስም አልፈቀደላቸውም፤ ፰ በሚስያም አጠገብ አልፈው ወደ ጢሮአዳ ወረዱ። ፱ ራእይም ለጳውሎስ በሌሊት ታየው፤ አንድ የመቄዶንያ ሰው። ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን እያለ ቆሞ ሲለምነው ነበር። ፲ ራእዩንም ካየ በኋላ ወዲያው ወደ መቄዶንያ ልንወጣ ፈለግን፥ ወንጌልን እንሰብክላቸው ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ጠራን መስሎናልና። ፲፩ ከጢሮአዳም ተነሥተን በቀጥታ ወደ ሳሞትራቄ በነገውም ወደ ናጱሌ በመርከብ ሄድን፤ ፲፪ ከዚያም ወደ ፊልጵስዩስ ደረስን፤ እርስዋም የመቄዶንያ ከተማ ሆና የወረዳ ዋና ከተማና ቅኝ አገር ናት፤ በዚህችም ከተማ አንዳንድ ቀን እንቀመጥ ነበር። ፲፫ በሰንበት ቀንም ከከተማው በር ውጭ የጸሎት ስፍራ በዚያ መሆኑን ስላሰብን ወደ ወንዝ አጠገብ ወጣን፤ ተቀምጠንም ለተሰበሰቡት ሴቶች ተናገርን። ፲፬ ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት። ፲፭ እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ። በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፥ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ ብላ ለመነችን፤ በግድም አለችን። ፲፮ ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን። ፲፯ እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች። የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኽ ነበር። ፲፰ ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን። ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ። ፲፱ ጌቶችዋም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ወጣ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ገበያ በሹማምት ፊት ጐተቱአቸው፤ ፳ ወደ ገዢዎችም አቅርበው። እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ። ፳፩ እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ አሉ። ፳፪ ሕዝቡም አብረው ተነሡባቸው፥ ገዢዎቹም ልብሳቸውን ገፈው በበትር ይመቱአቸው ዘንድ አዘዙ፤ ፳፫ በብዙም ከደበደቡአቸው በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፥ የወኅኒውንም ጠባቂ ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። ፳፬ እርሱም የዚህን ዓይነት ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ጣላቸው፥ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸው። ፳፭ በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፥ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር ፳፮ ድንገትም የወኅኒው መሠረት እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፤ በዚያን ጊዜም ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ የሁሉም እስራት ተፈታ። ፳፯ የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፥ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ። ፳፰ ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ። ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ ብሎ ጮኸ። ፳፱ መብራትም ለምኖ ወደ ውስጥ ሮጠ፥ እየተንቀጠቀጠም ከጳውሎስና ከሲላስ ፊት ተደፋ፤ ፴ ወደ ውጭም አውጥቶ። ጌቶች ሆይ፥ እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል? ኣላቸው። ፴፩ እነርሱም። በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ አሉት። ፴፪ ለእርሱና በቤቱም ላሉት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተናገሩአቸው። ፴፫ በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፥ ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ፤ ፴፬ ወደ ቤቱም አውጥቶ ማዕድ አቀረበላቸው፥ በእግዚአብሔርም ስላመነ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ሐሤት አደረገ። ፴፭ በነጋም ጊዜ ገዢዎቹ። እነዚያን ሰዎች ፍታቸው ብለው ሎሌዎቻቸውን ላኩ። ፴፮ የወኅኒውም ጠባቂ። ትፈቱ ዘንድ ገዢዎቹ ልከዋል፤ እንግዲህ አሁን ወጥታችሁ በሰላም ሂዱ ብሎ ይህን ቃል ለጳውሎስ ነገረው። ፴፯ ጳውሎስ ግን። እኛ የሮሜ ሰዎች ስንሆን ያለ ፍርድ በሕዝብ ፊት ደብድበው በወኅኒ ጣሉን፤ አሁንም በስውር ይጥሉናልን? አይሆንም ራሳቸው ግን መጥተው ያውጡን አላቸው። ፴፰ ሎሌዎቹም ይህን ነገር ለገዢዎች ነገሩ። የሮሜ ሰዎችም እንደ ሆኑ በሰሙ ጊዜ ፈሩ፤ ፴፱ መጥተውም ማለዱአቸው፥ አውጥተውም ከከተማ ይወጡ ዘንድ ለመኑአቸው። ፵ ከወኅኒውም ወጥተው ወደ ልድያ ቤት ገቡ፥ ወንድሞችንም ባዩ ጊዜ አጽናኑአቸውና ሄዱ።