፳፬
፩ ከአምስት ቀንም በኋላ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከሽማግሌዎችና ጠርጠሉስ ከሚሉት ከአንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ እነርሱም ስለ ጳውሎስ ለአገረ ገዡ አመለከቱት። ፪-፬ ነገር ግን እጅግ እንዳላቆይህ በቸርነትህ በአጭሩ ትሰማን ዘንድ እለምንሃለሁ። ፭ ይህ ሰው በሽታ ሆኖ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ ሁከት ሲያስነሣ፥ የመናፍቃን የናዝራውያን ወገን መሪ ሆኖ አግኝተነዋልና፤ ፮ መቅደስንም ደግሞ ሊያረክስ ሲሞክር ያዝነው፥ እንደ ሕጋችንም እንፈርድበት ዘንድ ወደድን። ፯ ነገር ግን የሻለቃው ሉስዮስ መጥቶ በብዙ ኃይል ከእጃችን ወሰደው፥ ፰ ከሳሾቹንም ወደ አንተ ይመጡ ዘንድ አዘዘ፤ አንተም ራስህ እርሱን መርምረህ እኛ ስለምንከስበት ነገር ሁሉ ልታውቅ ትችላለህ። ፱ አይሁድም ደግሞ። ይህ ነገር እንዲሁ ነው እያሉ ተስማሙ። ፲ ገዡም በጠቀሰው ጊዜ ጳውሎስ መለሰ እንዲህ ሲል። ከብዙ ዘመን ጀምረህ ለዚህ ሕዝብ አንተ ፈራጅ እንደ ሆንህ አውቃለሁና ደስ እያለኝ ስለ እኔ ነገር እመልሳለሁ፤ ፲፩ እሰግድ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ከወጣሁ ከአሥራ ሁለት ቀን እንዳይበልጥ ልታውቀው ትችላለህ። ፲፪ ከአንድም ስንኳ ስነጋገር ወይም ሕዝብን ስሰበስብ በመቅደስ ቢሆን በምኵራብም ቢሆን በከተማም ቢሆን አላገኙኝም። ፲፫ አሁንም ስለሚከሱኝ ያስረዱህ ዘንድ አይችሉም። ፲፬ ነገር ግን ይህን እመሰክርልሃለሁ፤ በሕጉ ያለውን በነቢያትም የተጻፉትን ሁሉ አምኜ የአባቶቼን አምላክ እነርሱ ኑፋቄ ብለው እንደሚጠሩት መንገድ አመልካለሁ፤ ፲፭ እነዚህም ራሳቸው ደግሞ የሚጠብቁት፥ ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ። ፲፮ ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ። ፲፯ ከብዙ ዓመትም በኋላ ለሕዝቤ ምጽዋትና መሥዋዕት አደርግ ዘንድ መጣሁ፤ ፲፰ ይህንም ሳደርግ ሳለሁ ሕዝብ ሳይሰበሰብ ሁከትም ሳይሆን በመቅደስ ስነጻ አገኙኝ። ፲፱ ነገር ግን በእኔ ላይ ነገር ያላቸው እንደ ሆነ፥ በፊትህ መጥተው ይከሱኝ ዘንድ የሚገባቸው ከእስያ የመጡ አንዳንድ አይሁድ አሉ። ፳-፳፪ ፊልክስ ግን የመንገዱን ነገር አጥብቆ አውቆአልና። የሻለቃው ሉስዮስ በወረደ ጊዜ ነገራችሁን እቆርጣለሁ ብሎ ወደ ፊት አዘገያቸው። ፳፫ የመቶውንም አለቃ ጳውሎስን ሲጠብቅ እንዲያደላለት፥ ከወዳጆቹም ማንም ሲያገለግለው ወይም ወደ እርሱ ሲመጣ እንዳይከለክልበት አዘዘው። ፳፬ ከጥቂት ቀንም በኋላ ፊልክስ አይሁዳዊት ከነበረች ድሩሲላ ከሚሉአት ከሚስቱ ጋር መጥቶ ጳውሎስን አስመጣ፥ በኢየሱስ ክርስቶስም ስለ ማመን የሚናገረውን ሰማው። ፳፭ እርሱም ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም ኵነኔ ሲነጋገር ሳለ፥ ፊልክስ ፈርቶ። አሁንስ ሂድ፥ በተመቸኝም ጊዜ ልኬ አስጠራሃለሁ ብሎ መለሰለት። ፳፮ ያን ጊዜም ደግሞ እንዲፈታው ጳውሎስ ገንዘብ ይሰጠው ዘንድ ተስፋ አደረገ፤ ስለዚህ ደግሞ ብዙ ጊዜ እያስመጣ ያነጋግረው ነበር። ፳፯ ሁለት ዓመትም ከሞላ በኋላ ጶርቅዮስ ፊስጦስ በፊልክስ ፈንታ ተተካ። ፊልክስም አይሁድን ደስ ያሰኝ ዘንድ ወዶ ጳውሎስን እንደ ታሰረ ተወው።