፩ ጌቶች ሆይ፥ እናንተ ደግሞ በሰማይ ጌታ እንዳላችሁ ታውቃላችሁና ለባሪያዎቻችሁ በጽድቅና በቅንነት አድርጉላቸው። ፪ ከማመስገን ጋር በጸሎት እየነቃችሁ ለእርሱ ትጉ። ፫ በዚያን ጊዜም ስለ እርሱ ደግሞ የታሰርሁበትን የክርስቶስን ምሥጢር እንድንነግር እግዚአብሔር የቃሉን ደጅ ይከፍትልን ዘንድ ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ። ፬ ልናገር እንደሚገባኝ ያህል እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ። ፭ ዘመኑን እየዋጃችሁ፥ በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ። ፮ ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን። ፯ የተወደደ ወንድምና የታመነ አገልጋይ በጌታም አብሮኝ ባሪያ የሆነ ቲኪቆስ ኑሮዬን ሁሉ ያስታውቃችኋል። ፰-፲፪ ከእናንተ የሆነ የክርስቶስ ባሪያ ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ተረድታችሁና ፍጹማን ሆናችሁ እንድትቆሙ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ በጸሎቱ ይጋደላል። ፲፫ ስለ እናንተ በሎዶቅያም በኢያራ ከተማም ስላሉቱ እጅግ እንዲቀና እመሰክርለታለሁና። ፲፬ የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ ዴማስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ፲፭ በሎዶቅያ ላሉቱ ወንድሞችና ለንምፉን በቤቱም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልን። ፲፮ ይህችም መልእክት በእናንተ ዘንድ ከተነበበች በኋላ፥ በሎዶቅያ ሰዎች ማኅበር ደግሞ እንድትነበብ አድርጉ። ከሎዶቅያም የምትገኘውን መልእክት እናንተ ደግሞ አንብቡ። ፲፯ ለአክሪጳም። በጌታ የተቀበልኸውን አገልግሎት እንድትፈጽሙው ተጠንቀቅ በሉልኝ። ፲፰ በገዛ እጄ የተጻፈ የእኔ የጳውሎስ ሰላምታ ይህ ነው። እስራቴን አስቡ። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።