፩ የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? ፪ ይህን ብቻ ከእናንተ እንድማር እወዳለሁ፤ በሕግ ሥራ ወይም ከእምነት ጋር በሆነ መስማት መንፈስን ተቀበላችሁን? ፫ እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጽማላችሁን? ፬ በውኑ ከንቱ እንደ ሆነስ እንደዚህ ያለ መከራ በከንቱ ተቀበላችሁን? ፭ እንግዲህ መንፈስን የሚሰጣችሁ በእናንተም ዘንድ ተአምራት የሚያደርግ፥ በሕግ ሥራ ነውን ወይስ ከእምነት ጋር በሆነ መስማት ነው? ፮ እንዲሁ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። ፯ እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ። ፰ መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ። በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ። ፱ እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ። ፲ ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና። ፲፩ ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎአልና ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው። ፲፪ ሕግም ከእምነት አይደለም ነገር ግን። የሚያደርገው ይኖርበታል ተብሎአል። ፲፫ በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤ ፲፬ የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ። ፲፭ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። የሰው ስንኳ ቢሆን እርግጠኛውን ኪዳን ማንም አይንቅም ወይም አይጨምርበትም። ፲፮ ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር። ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን። ለዘርህም ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ። ፲፯ ይህንም እላለሁ፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠውን ኪዳን የተስፋውን ቃል እስኪሽር ድረስ አያፈርስም። ፲፰ ርስቱ በሕግ ቢሆንስ እንግዲያስ በተስፋ ቃል አይሆንም፤ በተስፋ ቃል ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶአል። ፲፱ እንግዲህ ሕግ ምንድር ነው? ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ። ፳ መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። ፳፩ እንግዲህ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የሚቃወም ነውን? አይደለም። ሕያው ሊያደርግ የሚቻለው ሕግ ተሰጥቶ ቢሆንስ በእውነት ጽድቅ ከሕግ በሆነ ነበር፤ ፳፪ ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመን የሆነው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ ይሰጥ ዘንድ መጽሐፍ ከኃጢአት በታች ሁሉን ዘግቶታል። ፳፫ እምነትም ሳይመጣ ሊገለጥ ላለው እምነት ተዘግተን ከሕግ በታች እንጠበቅ ነበር። ፳፬ እንደዚህ በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኖአል፤ ፳፭ እምነት ግን መጥቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም። ፳፮ በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ ፳፯ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና። ፳፰ አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና። ፳፱ እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።