፩ ፊተኛይቱም ደግሞ የአገልግሎት ስርዓትና የዚህ ዓለም የሆነው መቅደስ ነበራት። ፪ የመጀመሪያይቱ ድንኳን ተዘጋጅታ ነበርና፥ በእርስዋም ቅድስት በምትባለው ውስጥ መቅረዙና ጠረጴዛው የመስዋዕቱም ኅብስት ነበረባት፤ ፫ ከሁለተኛውም መጋረጃ ወዲያ ቅድስተ ቅዱሳን የምትባለው ድንኳን ነበረች፥ ፬ በዚያም ውስጥ የወርቅ ማዕጠንት ነበረ ሁለንተናዋም በወርቅ የተለበጠች የኪዳን ታቦት፤ በእርስዋም ውስጥ መና ያለባት የወርቅ መሶብና የበቀለች የአሮን በትር የኪዳኑም ጽላት ነበሩ፥ ፭ በላይዋም ማስተስሪያውን የሚጋርዱ የክብር ኪሩቤል ነበሩ፤ ስለ እነዚህም ስለ እያንዳንዳቸው ልንናገር አሁን አንችልም። ፮ ይህም እንደዚህ ተዘጋጅቶ ሳለ፥ ካህናት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ይገቡባታል፤ ፯ በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፥ እርሱም ሰለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ስሕተት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም፤ ፰ ፊተኛይቱም ድንኳን በዚህ ገና ቆማ ሳለች፥ ወደ ቅድስት የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል። ፱-፲፩ ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥ በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥ ፲፪ የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። ፲፫ የኮርማዎችና የፍየሎች ደም በረከሱትም ላይ የተረጨ የጊደር አመድ ሥጋን ለማንጻት የሚቀድሱ ከሆኑ፥ ፲፬ ነውር የሌለው ሆኖ በዘላለም መንፈስ ራሱን ለእግዚአብሔር ያቀረበ የክርስቶስ ደም እንዴት ይልቅ ሕያውን እግዚአብሔርን ልታመልኩ ከሞተ ሥራ ሕሊናችሁን ያነጻ ይሆን? ፲፭ ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው። ፲፮ ኑዛዜ ያለ እንደሆነ የተናዛዡን ሞት ማርዳት የግድ ነውና፤ ፲፯ ሰው ሲሞት ኑዛዜው ይጸናልና፥ ተናዛዡ በሕይወት ሲኖር ግን ከቶ አይጠቅምም። ፲፰ ስለዚህም ፊተኛው ኪዳን እንኳ ያለ ደም አልተመረቀም። ፲፱-፳፩ እንዲሁም በድንኳኒቱና በማገልገያው ዕቃ ሁሉ ደምን ረጨ። ፳፪ እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፥ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም። ፳፫ እንግዲህ በሰማያት ያሉትን የሚመስለው ነገር በዚህ ሊነጻ እንጂ በሰማያት ያሉቱ ራሳቸው ከእርሱ ይልቅ በሚበልጥ መስዋዕት ሊነጹ የግድ ነበረ። ፳፬ ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ። ፳፭ ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ ፳፮ እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል። ፳፯ ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው፥ ፳፰ እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል።