፩ ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፥ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም ከቶ አይችልም። ፪ እንደዚህማ ባይሆን፥ የሚያመልኩት አንድ ጊዜ ነጽተው ከዚያ በኋላ በሕሊናቸው ኃጢአትን ስላላወቁ ማቅረብን በተዉ አልነበረምን? ፫ ነገር ግን በዚያ መሥዋዕት በየዓመቱ የኃጢአት መታሰቢያ አለ፤ ፬ የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና። ፭ ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ። መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤ ፮ በሙሉ በሚቃጠል መሥዋዕትና ሰለ ኃጢአት በሚሰዋ መሥዋዕት ደስ አላለህም። ፯ በዚያን ጊዜ። እነሆ፥ በመጽሐፍ ጥቅልል ስለ እኔ እንደ ተጻፈ፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ አልሁ ፰ ይላል። በዚህ ላይ። መሥዋዕትንና መባን በሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕትንም ስለ ኃጢአትም የሚሰዋ መሥዋዕትን አልወደድህም በእርሱም ደስ አላለህም ብሎ፥ እነዚህም እንደ ሕግ የሚቀርቡት ናቸው፥ ፱ ቀጥሎ። እነሆ፥ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ላደርግ መጥቼአለሁ ብሎአል። ሁለተኛውንም ሊያቆም የፊተኛውን ይሽራል። ፲ በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል። ፲፩ ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፤ ፲፪ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፥ ፲፫ ጠላቶቹም የእግሩ መረገጫ እስኪደረጉ ድረስ ወደ ፊት ይጠብቃል። ፲፬ አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋልና። ፲፭-፲፯ ብሎ ከተናገረ በኋላ፥ ኃጢአታቸውንና ዓመጻቸውንም ደግሜ አላስብም ይላል። ፲፰ የእነዚህም ስርየት ባለበት ዘንድ፥ ከዚህ ወዲህ ስለ ኃጢአት ማቅረብ የለም። ፲፱-፳፩ በእግዚአብሔርም ቤት ላይ የሆነ ታላቅ ካህን ስላለን፥ ፳፪ ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ፤ ፳፫ የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ፤ ፳፬ ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ ፳፭ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ። ፳፮ የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና፥ ፳፯ የሚያስፈራ ግን የፍርድ መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት አለ። ፳፰ የሙሴን ሕግ የናቀ ሰው ሁለት ወይም ሦስት ቢመሰክሩበት ያለ ርኅራኄ ይሞታል፤ ፳፱ የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር የቆጠረ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ፥ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል? ፴ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ያለውን እናውቃለንና፤ ደግሞም። ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል። ፴፩ በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው። ፴፪-፴፬ የሚበልጥና ለዘወትር የሚኖር ገንዘብ በሰማይ ራሳችሁ እንዳላችሁ አውቃችሁ፥ በእስራቴ ራራችሁልኝ የገንዘባችሁንም ንጥቂያ በደስታ ተቀበላችሁ። ፴፭ እንግዲህ ታላቅ ብድራት ያለውን ድፍረታችሁን አትጣሉ። ፴፮ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። ፴፯ ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፥ ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም፤ ፴፰ ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፥ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም። ፴፱ እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም።