፩ ጢባርዮስ ቄሣርም በነገሠ በአሥራ አምስተኛይቱ ዓመት፥ ጴንጤናዊው ጲላጦስም በይሁዳ ሲገዛ፥ ሄሮድስም በገሊላ የአራተኛው ክፍል ገዥ፥ ወንድሙ ፊልጶስም በኢጡርያስ በጥራኮኒዶስም አገር የአራተኛው ክፍል ገዥ፥ ሊሳኒዮስም በሳቢላኒስ የአራተኛው ክፍል ገዥ ሆነው ሳሉ፥ ፪ ሐናና ቀያፋም ሊቃነ ካህናት ሳሉ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ። ፫-፯ ስለዚህ ከእርሱ ሊጠመቁ ለወጡት ሕዝብ እንዲህ ይላቸው ነበር። እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? ፰ እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም። አብርሃም አባት አለን ማለትን አትጀምሩ፤ ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር እንዲችል እላችኋለሁና። ፱ አሁንስ ምሳር ደግሞ በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። ፲ ሕዝቡም። እንግዲህ ምን እናድርግ? ብለው ይጠይቁት ነበር። ፲፩ መልሶም። ሁለት ልብስ ያለው ለሌለው ያካፍል፥ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ ይል ነበር። ፲፪ ቀራጮችም ደግሞ ሊጠመቁ መጥተው። መምህር ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉት። ፲፫ ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ አላቸው። ፲፬ ጭፍሮችም ደግሞ። እኛ ደግሞ ምን እናድርግ? ብለው ይጠይቁት ነበር። እርሱም። በማንም ግፍ አትሥሩ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፥ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ አላቸው። ፲፭ ሕዝቡም ሲጠብቁ ሳሉ ሁሉም በልባቸው ስለ ዮሐንስ። ይህ ክርስቶስ ይሆንን? ብለው ሲያስቡ ነበር፥ ፲፮ ዮሐንስ መልሶ። እኔስ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት ከማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ ፲፯ መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል አላቸው። ፲፰ ስለዚህ ሕዝቡን በብዙ ሌላ ምክር እየመከራቸው ወንጌልን ይሰብክላቸው ነበር፤ ፲፱ የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ ግን፥ ስለ ሄሮድያዳ ስለ ወንድሙ ስለ ፊልጶስ ሚስትና ሄሮድስ ስላደረገው ሌላ ክፋት ሁሉ ዮሐንስ ስለ ገሠጸው፥ ፳ ይህን ደግሞ ከሁሉ በላይ ጨምሮ ዮሐንስን በወኅኒ አገባው። ፳፩ ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፥ ፳፪ መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፥ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ። ፳፫ ኢየሱስም ሊያስተምር ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል ሆኖት ነበር እንደመሰላቸው የዮሴፍ ልጅ ሆኖ፥ የኤሊ ልጅ፥ ፳፬ የማቲ ልጅ፥ የሌዊ ልጅ፥ የሚልኪ ልጅ፥ ፳፭ የዮና ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ የማታትዩ ልጅ፥ የአሞጽ ልጅ፥ የናሆም ልጅ፥ የኤሲሊም ልጅ ፳፮ የናጌ ልጅ፥ የማአት ልጅ፥ የማታትዩ ልጅ የሴሜይ ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ ፳፯ የዮዳ ልጅ፥ የዮናን ልጅ፥ የሬስ ልጅ፥ የዘሩባቤል ልጅ፥ የሰላትያል ልጅ፥ የኔሪ ልጅ፥ ፳፰ የሚልኪ ልጅ፥ የሐዲ ልጅ፥ የዮሳስ ልጅ፥ የቆሳም ልጅ፥ የኤልሞዳም ልጅ፥ የኤር ልጅ፥ ፳፱ የዮሴዕ ልጅ፥ የኤልዓዘር ልጅ የዮራም ልጅ፥ የማጣት ልጅ፥ የሌዊ ልጅ፥ ፴ የስምዖን ልጅ፥ የይሁዳ ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ ፴፩ የዮናን ልጅ፥ የኤልያቄም ልጅ፥ የሜልያ ልጅ፥ የማይናን ልጅ፥ የማጣት ልጅ፥ የናታን ልጅ ፴፪ የዳዊት ልጅ፥ የእሴይ ልጅ፥ የኢዮቤድ ልጅ፥ የቦዔዝ ልጅ፥ የሰልሞን ልጅ፥ ፴፫ የነአሶን ልጅ፥ የአሚናዳብ ልጅ፥ የአራም ልጅ፥ የአሮኒ ልጅ፥ የኤስሮም ልጅ፥ ፴፬ የፋሬስ ልጅ፥ የይሁዳ ልጅ፥ የያዕቆብ ልጅ፥ የይስሐቅ ልጅ፥ የአብርሃም ልጅ፥ የታራ ልጅ፥ ፴፭ የናኮር ልጅ፥ የሴሮህ ልጅ፥ የራጋው ልጅ፥ የፋሌቅ ልጅ፥ የአቤር ልጅ፥ የሳላ ልጅ፥ ፴፮ የቃይንም ልጅ፥ የአርፋክስድ ልጅ፥ የሴም ልጅ፥ የኖኅ ልጅ፥ የላሜህ ልጅ፥ ፴፯ የማቱሳላ ልጅ፥ የሄኖክ ልጅ፥ የያሬድ ልጅ፥ ፴፰ የመላልኤል ልጅ፥ የቃይናን ልጅ፥ የሄኖስ ልጅ፥ የሴት ልጅ፥ የአዳም ልጅ፥ የእግዚአብሔር ልጅ።