፲፫
፩ በዚያን ጊዜም ሰዎች መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስላደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች አወሩለት። ፪ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ስለ ደረሰባቸው ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሉአችኋልን? ፫ እላችኋለሁ፥ አይደለም፤ ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ። ፬ ወይስ በሰሌሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ አሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን? አይደለም፥ እላችኋለሁ፤ ፭ ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ። ፮ ይህንም ምሳሌ አለ። ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፥ ፍሬም ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም። ፯ የወይን አትክልት ሠራተኛውንም። እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም፤ ቍረጣት፤ ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቍላለች? አለው። ፰ እርሱ ግን መልሶ። ጌታ ሆይ፥ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት። ፱ ወደ ፊትም ብታፈራ፥ ደኅና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ አለው። ፲ በሰንበትም በአንድ ምኵራብ ያስተምር ነበር። ፲፩ እነሆም፥ ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ የድካም መንፈስ ያደረባት ሴት ነበረች፥ እርስዋም ጐባጣ ነበረች ቀንታም ልትቆም ከቶ አልተቻላትም። ፲፪ ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና። አንቺ ሴት፥ ከድካምሽ ተፈትተሻል አላት፥ እጁንም ጫነባት፤ ፲፫ ያን ጊዜም ቀጥ አለች፥ እግዚአብሔርንም አመሰገነች። ፲፬ የምኵራብ አለቃ ግን ኢየሱስ በሰንበት ስለ ፈወሰ ተቈጥቶ መለሰና ሕዝቡን። ሊሠራባቸው የሚገባ ስድስት ቀኖች አሉ፤ እንግዲህ በእነርሱ መጥታችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት አይደለም አለ። ፲፭ ጌታም መልሶ። እናንተ ግብዞች፥ ከእናንተ እያንዳንዱ በሰንበት በሬውን ወይስ አህያውን ከግርግሙ ፈትቶ ውኃ ሊያጠጣው ይወስደው የለምን? ፲፮ ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሰራት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው። ፲፯ ይህንም ሲናገር ሳለ የተቃወሙት ሁሉ አፈሩ፤ ከእርሱም በተደረገው ድንቅ ሁሉ ሕዝቡ ሁሉ ደስ አላቸው። ፲፰ እርሱም። የእግዚአብሔር መንግሥት ምን ትመስላለች፥ በምንስ አስመስላታለሁ? ፲፱ ሰው ወስዶ በአትክልቱ የጣላትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ አደገችም ታላቅ ዛፍም ሆነች፥ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ ሰፈሩ አለ። ፳ ደግሞም፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን አስመስላታለሁ? ፳፩ ሴት ወስዳ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች አለ። ፳፪ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ከተማዎችንና መንደሮችን እያስተማረ ያልፍ ነበር። ፳፫ አንድ ሰውም። ጌታ ሆይ፥ የሚድኑ ጥቂቶች ናቸውን? አለው። እርሱም እንዲህ አላቸው። ፳፬ በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ፤ እላችኋለሁና፥ ብዙዎች ሊገቡ ይፈልጋሉ አይችሉምም። ፳፭ ባለቤቱ ተነሥቶ በሩን ከቈለፈ በኋላ፥ እናንተ በውጭ ቆማችሁ። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን እያላችሁ በሩን ልታንኳኩ ትጀምራላችሁ እርሱም መልሶ። ከወዴት እንደ ሆናችሁ አላውቃችሁም ይላችኋል። ፳፮ በዚያን ጊዜም። በፊትህ በላን ጠጣንም በአደባባያችንም አስተማርህ ልትሉ ትጀምራላችሁ፤ ፳፯ እርሱም። እላችኋለሁ፥ ከወዴት እንደ ሆናችሁ አላውቃችሁም፤ ሁላችሁ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ይላችኋል። ፳፰ አብርሃምንና ይስሐቅን ያዕቆብንም ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ባያችሁ ጊዜ፥ እናንተ ግን ወደ ውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ፥ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ፳፱ ከምሥራቅና ከምዕራብም ከሰሜንና ከደቡብም ይመጣሉ፥ በእግዚአብሔርም መንግሥት በማዕድ ይቀመጣሉ። ፴ እነሆም፥ ከኋለኞች ፊተኞች የሚሆኑ አሉ፥ ከፊተኞችም ኋለኞች የሚሆኑ አሉ። ፴፩ በዚያን ሰዓት ከፈሪሳውያን አንዳንዱ ቀርበው። ሄሮድስ ሊገድልህ ይወዳልና ከዚህ ውጣና ሂድ አሉት። ፴፪ እንዲህም አላቸው። ሄዳችሁ ለዚያች ቀበሮ። እነሆ፥ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ በሽተኞችንም እፈውሳለሁ፥ በሦስተኛውም ቀን እፈጸማለሁ በሉአት። ፴፫ ዳሩ ግን ነቢይ ከኢየሩሳሌም ውጭ ይጠፋ ዘንድ አይገባውምና ዛሬና ነገ ከነገ በስቲያም ልሄድ ያስፈልገኛል። ፴፬ ኢየሩሳሌም፥ ኢየሩሳሌም፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ፥ እናንተም አልወደዳችሁም። ፴፭ እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል። እላችኋለሁም፥ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።