፲፮
፩ ደግሞም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ። መጋቢ የነበረው አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፥ በእርሱ ዘንድ። ይህ ሰው ያለህን ይበትናል ብለው ከሰሱት። ፪ ጠርቶም። ይህ የምሰማብህ ምንድር ነው? ወደ ፊት ለእኔ መጋቢ ልትሆን አትችልምና የመጋቢነትህን ሂሳብ አስረክበኝ አለው። ፫ መጋቢውም በልቡ። ጌታዬ መጋቢነቱን ከእኔ ይወስዳልና ምን ላድርግ? ለመቈፈር ኃይል የለኝም፥ መለመንም አፍራለሁ። ፬ ከመጋቢነቱ ብሻር በቤታቸው እንዲቀበሉኝ የማደርገውን አውቃለሁ አለ። ፭ የጌታውንም ባለ ዕዳዎች እያንዳንዳቸውን ጠርቶ የፊተኛውን። ለጌታዬ ምን ያህል ዕዳ አለብህ? አለው። ፮ እርሱም። መቶ ማድጋ ዘይት አለ። ደብዳቤህን እንካ ፈጥነህም ተቀምጠህ አምሳ ብለህ ጻፍ አለው። ፯ በኋላም ሌላውን። አንተስ ስንት ዕዳ አለብህ? አለው። እርሱም። መቶ ጫን ስንዴ አለ። ደብዳቤህን እንካ ሰማንያ ብለህም ጻፍ አለው። ፰ ጌታውም ዓመፀኛውን መጋቢ በልባምነት ስላደረገ አመሰገነው የዚህ ዓለም ልጆች ለትውልዳቸው ከብርሃን ልጆች ይልቅ ልባሞች ናቸውና። ፱ እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ፲ ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው፥ ከሁሉ በሚያንስም የሚያምፅ በብዙ ደግሞ ዓመፀኛ ነው። ፲፩ እንግዲያስ በዓመፃ ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ እውነተኛውን ገንዘብ ማን አደራ ይሰጣችኋል? ፲፪ በሌላ ሰው ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ የእናንተን ማን ይሰጣችኋል? ፲፫ ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ባርያ ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላልና ሁለተኛውንም ይወዳል፥ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል። ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ፲፬ ገንዘብንም የሚወዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው ያፌዙበት ነበር። ፲፭ እንዲህም አላቸው። ራሳችሁን በሰው ፊት የምታጸድቁ እናንተ ናችሁ፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ልባችሁን ያውቃል፤ በሰው ዘንድ የከበረ በእግዚአብሔር ፊት ርኵሰት ነውና። ፲፮ ሕግና ነቢያት እስከ ዮሐንስ ነበሩ፤ ከዚያ ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት ይሰበካል፤ ሁሉም ወደ እርስዋ በኃይል ይገቡባታል። ፲፯ ነገር ግን ከሕግ አንዲት ነጥብ ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ሊያልፍ ይቀላል። ፲፰ ሚስቱንም የሚፈታ ሁሉ ሌላይቱንም የሚያገባ ያመነዝራል፥ ከባልዋም የተፈታችውን የሚያገባ ያመነዝራል። ፲፱ ቀይ ልብስና ቀጭን የተልባ እግር የለበሰ አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፥ ዕለት ዕለትም እየተመቸው በደስታ ይኖር ነበር። ፳ አልዓዛርም የሚባል አንድ ድሀ በቍስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፥ ፳፩ ከባለ ጠጋውም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ሊጠግብ ይመኝ ነበር፤ ውሾች እንኳ መጥተው ቍስሎቹን ይልሱ ነበር። ፳፪ ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ባለ ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ። ፳፫ በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ። ፳፬ እርሱም እየጮኸ። አብርሃም አባት ሆይ፥ ማረኝ፥ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ አለ። ፳፭ አብርሃም ግን። ልጄ ሆይ፥ አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል አንተም ትሣቀያለህ። ፳፮ ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፥ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል አለ። ፳፯ እርሱም። እንኪያስ፥ አባት ሆይ፥ ወደ አባቴ ቤት እንድትሰደው እለምንሃለሁ፤ አምስት ወንድሞች አሉኝና፤ ፳፰ እነርሱ ደግሞ ወደዚህ ሥቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ይመስክርላቸው አለ። ፳፱ አብርሃም ግን። ሙሴና ነቢያት አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙ አለው። ፴ እርሱም። አይደለም፥ አብርሃም አባት ሆይ፥ ነገር ግን ከሙታን አንዱ ቢሄድላቸው ንስሐ ይገባሉ አለ። ፴፩ ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ፥ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም አለው።