፲፱
፩-፫ ኢየሱስንም የትኛው እንደ ሆነ ሊያይ ይፈልግ ነበር፤ ቁመቱም አጭር ነበረና ስለ ሕዝቡ ብዛት አቃተው። ፬ በዚያችም መንገድ ያልፍ ዘንድ አለውና ያየው ዘንድ ወደ ፊት ሮጦ በአንድ ሾላ ላይ ወጣ። ፭ ኢየሱስም ወደዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ፥ አሻቅቦ አየና። ዘኬዎስ ሆይ፥ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ አለው። ፮ ፈጥኖም ወረደ በደስታም ተቀበለው። ፯ ሁሉም አይተው። ከኃጢአተኛ ሰው ጋር ሊውል ገባ ብለው አንጐራጐሩ። ፰ ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን። ጌታ ሆይ፥ ካለኝ ሁሉ እኵሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደ ሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ አለው። ፱ ኢየሱስም። እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል፤ ፲ የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና አለው። ፲፩ እነርሱም ይህን ሲሰሙ፥ ወደ ኢየሩሳሌም መቅረቡ ስለ ሆነ የእግዚአብሔርም መንግሥት ፈጥኖ ሊገለጥ እንዳለው ስለ መሰላቸው ምሳሌ ጭምር ተናገረ። ፲፪ ስለዚህም እንዲህ አላቸው። አንድ መኰንን ለራሱ መንግሥትን ይዞ ሊመለሰ ወደ ሩቅ አገር ሄደ። ፲፫ አሥር ባሪያዎችንም ጠርቶ አሥር ምናን ሰጣቸውና። እስክመጣ ድረስ ነግዱ አላቸው። ፲፬ የአገሩ ሰዎች ግን ይጠሉት ነበርና። ይህ በላያችን ሊነግሥ አንወድም ብለው በኋላው መልክተኞችን ላኩ። ፲፭ መንግሥትንም ይዞ በተመለሰ ጊዜ፥ ገንዘብ የሰጣቸውን እነዚህን ባሪያዎች ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ያውቅ ዘንድ እንዲጠሩለት አዘዘ። ፲፮ የፊተኛውም ደርሶ። ጌታ ሆይ፥ ምናንህ አሥር ምናን አተረፈ አለው። ፲፯ እርሱም። መልካም፥ አንተ በጎ ባሪያ፥ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በአሥር ከተማዎች ላይ ሥልጣን ይሁንልህ አለው። ፲፰ ሁለተኛውም መጥቶ። ጌታ ሆይ፥ ምናንህ አምስት ምናን አተረፈ አለው። ፲፱ ይህንም ደግሞ። አንተም በአምስት ከተማዎች ላይ ሁን አለው። ፳ ሌላውም መጥቶ። ጌታ ሆይ፥ በጨርቅ ጠቅልዬ የጠበቅኋት ምናንህ እነሆ፤ ፳፩ ፈርቼሃለሁና፥ ጨካኝ ሰው ስለ ሆንህ፤ ያላኖርኸውን ትወስዳለህ ያልዘራኸውንም ታጭዳለህ አለው። ፳፪ እርሱም። አንተ ክፉ ባሪያ፥ አፍህ በተናገረው እፈርድብሃለሁ። እኔ ያላኖርሁትን የምወስድና ያልዘራሁትን የማጭድ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ አወቅህ፤ ምን ነው ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ያልሰጠኸው? ፳፫ እኔም መጥቼ ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር አለው። ፳፬ በዚያም ቆመው የነበሩትን። ምናኑን ውሰዱበት አሥሩ ምናን ላለውም ስጡት አላቸው። ፳፭ እነርሱም። ጌታ ሆይ፥ አሥር ምናን አለው አሉት። ፳፮ እላችኋለሁ፥ ላለው ሁሉ ይሰጠዋል፥ ከሌለው ግን ያው ያለው ስንኳ ይወሰድበታል። ፳፯ ነገር ግን እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡአቸው በፊቴም እረዱአቸው። ፳፰ ይህንም ከተናገረ በኋላ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ይቀድማቸው ነበር። ፳፱ ደብረ ዘይትም በሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከና። ፴ በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ ወደ እርስዋም ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፥ ፈትታችሁም አምጡት። ፴፩ ማንም። ስለ ምን ትፈቱታላችሁ? ብሎ ቢጠይቃችሁ፥ እንዲሁ። ለጌታ ያስፈልገዋል በሉ አላቸው። ፴፪ የተላኩትም ሄደው እንዳላቸው አገኙ። ፴፫ እነርሱም ውርንጫውን ሲፈቱ ጌቶቹ። ውርንጫውን ስለ ምን ትፈቱታላችሁ? አሉአቸውም ፴፬ እነርሱም። ለጌታ ያስፈልገዋል አሉ። ፴፭ ወደ ኢየሱስም አመጡት፥ በውርንጫውም ላይ ልብሳቸውን ጭነው ኢየሱስን አስቀመጡት። ፴፮ ሲሄድም ልብሳቸውን በመንገድ ያነጥፉ ነበር። ፴፯ ወደ ደብረ ዘይት ቍልቍለትም አሁን በቀረበ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ሁላቸው ደስ እያላቸው ተአምራትን ሁሉ ስላዩ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን ሊያመሰግኑ ጀምረው። ፴፰ በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው፤ በሰማይ ሰላም በአርያምም ክብር አሉ። ፴፱ ከሕዝብም መካከል ከፈሪሳውያን አንዳንዱ። መምህር ሆይ፥ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት። ፵ መልሶም። እላችኋለሁ፥ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ አላቸው። ፵፩ ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፥ ፵፪ እንዲህ እያለ። ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል። ፵፫ ወራት ይመጣብሻልና፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ ፵፬ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና። ፵፭ ወደ መቅደስም ገብቶ በእርሱ የሚሸጡትን የሚገዙትንም ያወጣ ጀመር፤ ፵፮ እርሱም። ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት አላቸው። ፵፯ ዕለት ዕለትም በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች የሕዝቡ ታላላቆችም ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፥ ፵፰ የሚያደርጉበትንም አጡ፤ ሕዝቡ ሁሉ ሲሰሙት ተንጠልጥለውበት ነበርና።