፳፪
፩ ፋሲካም የሚባለው የቂጣ በዓል ቀረበ። ፪ የካህናት አለቆችና ጻፎችም እንዴት እንዲያጠፉት ይፈልጉ ነበር፤ ሕዝቡን ይፈሩ ነበርና። ፫ ሰይጣንም ከአሥራ ሁለቱ ቍጥር አንዱ በነበረው የአስቆሮቱ በሚባለው በይሁዳ ገባ፤ ፬ ሄዶም እንዴት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ከካህናት አለቆችና ከመቅደስ አዛዦች ጋር ተነጋገረ። ፭ እነርሱም ደስ አላቸው፥ ገንዘብም ሊሰጡት ተዋዋሉ። ፮ እሺም አለ፥ ሕዝብም በሌለበት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። ፯ ፋሲካንም ሊያርዱበት የሚገባው የቂጣ በዓል ደረሰ፤ ፰ ጴጥሮስንና ዮሐንስንም። ፋሲካን እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን ብሎ ላካቸው። ፱ እነርሱም። ወዴት እናዘጋጅ ዘንድ ትወዳለህ? አሉት። ፲ እርሱም አላቸው። እነሆ፥ ወደ ከተማ ስትገቡ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደ ሚገባበት ቤት ተከተሉት፤ ፲፩ ለባለቤቱም። መምህሩ። ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል በሉት፤ ፲፪ ያም በደርብ ላይ ያለውን የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን። ፲፫ ሄደውም እንዳላቸው አገኙና ፋሲካን አሰናዱ። ፲፬ ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማዕድ ተቀመጠ። ፲፭ እርሱም። ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤ ፲፮ እላችኋለሁና፥ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደ ፊት ከዚህ አልበላም አላቸው። ፲፯ ጽዋንም ተቀበለ አመስግኖም። ይህን እንካችሁ በመካከላችሁም ተካፈሉት፤ ፲፰ እላችኋለሁና፥ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከአሁን ጀምሮ ከወይኑ ፍሬ አልጠጣም አለ። ፲፱ እንጀራንም አንሥቶ አመሰገነ ቆርሶም ሰጣቸውና። ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። ፳ እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ። ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው። ፳፩ ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ እጅ እነሆ በማዕድ ከእኔ ጋር ናት። ፳፪ የሰው ልጅስ እንደ ተወሰነው ይሄዳል፥ ነገር ግን አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት። ፳፫ ከእነርሱም ይህን ሊያደርግ ያለው ማን እንደ ሆነ እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር። ፳፬ ደግሞም ማናቸውም ታላቅ ሆኖ እንዲቈጠር በመካከላቸው ክርክር ሆነ። ፳፭ እንዲህም አላቸው። የአሕዛብ ነገሥታት ይገዙአቸዋል፥ በላያቸውም የሚሠለጥኑት ቸርነት አድራጊዎች ይባላሉ። ፳፮ እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፥ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን። ፳፯ በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው? የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ። ፳፰ ነገር ግን እናንተ በፈተናዎቼ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ፤ ፳፱-፴፩ ጌታም። ስምዖን ስምዖን ሆይ፥ እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ ፴፪ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና አለ። ፴፫ እርሱም። ጌታ ሆይ፥ ወደ ወኅኒም ወደ ሞትም ከአንተ ጋር ለመሄድ የተዘጋጀሁ ነኝ አለው። ፴፬ እርሱ ግን። ጴጥሮስ ሆይ፥ እልሃለሁ፥ እንዳታውቀኝ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዛሬ ዶሮ አይጮኽም አለው። ፴፭ ደግሞም። ያለ ኮረጆና ያለ ከረጢት ያለ ጫማም በላክኋችሁ ጊዜ፥ አንዳች ጐደለባችሁን? አላቸው። እነርሱም። አንዳች እንኳ አሉ። ፴፮ እርሱም። አሁን ግን ኮረጆ ያለው ከእርሱ ጋር ይውሰድ፥ ከረጢትም ያለው እንዲሁ፤ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ሰይፍ ይግዛ። ፴፯ እላችኋለሁና፥ ይህ። ከዓመፀኞች ጋር ተቈጠረ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ሊፈጸም ግድ ነው፤ አዎን፥ ስለ እኔ የሚሆነው አሁን ይፈጸማልና አላቸው። ፴፰ እነርሱም። ጌታ ሆይ፥ እነሆ፥ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ አሉት። እርሱም። ይበቃል አላቸው። ፴፱ ወጥቶም እንደ ልማዱ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ደግሞ ተከተሉት። ፵ ወደ ስፍራውም ደርሶ። ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ አላቸው። ፵፩ ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ የሚያህል ራቀ፥ ተንበርክኮም። አባት ሆይ፥ ፵፪ ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። ፵፫ ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታ መልአክ ታየው። ፵፬ በፍርሃትም ሲጣጣር አጽንቶ ይጸልይ ነበር፤ ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ። ፵፭ ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣና ከኀዘን የተነሣ ተኝተው ሲያገኛቸው። ፵፮ ስለ ምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ አላቸው። ፵፯ ገናም ሲናገር እነሆ፥ ሰዎች መጡ፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱም ይሁዳ የሚባለው ይቀድማቸው ነበር፥ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ቀረበ። ፵፰ ኢየሱስ ግን። ይሁዳ ሆይ፥ በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን? አለው። ፵፱ በዙሪያውም የነበሩት የሚሆነውን ባዩ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ በሰይፍ እንምታቸውን? አሉት። ፶ ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው። ፶፩ ኢየሱስ ግን መልሶ። ይህንስ ፍቀዱ አለ፤ ጆሮውንም ዳስሶ ፈወሰው። ፶፪ ኢየሱስም ወደ እርሱ ለመጡበት ለካህናት አለቆችና ለመቅደስ አዛዦች ለሽማግሌዎችም። ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ወጣችሁን? ፶፫ በመቅደስ ዕለት ዕለት ከእናንተ ጋር ስሆን እጆቻችሁን አልዘረጋችሁብኝም፤ ይህ ግን ጊዜያችሁና የጨለማው ሥልጣን ነው አላቸው። ፶፬ ይዘውም ወሰዱት ወደ ሊቀ ካህናት ቤትም አገቡት፤ ጴጥሮስም ርቆ ይከተለው ነበር። ፶፭ በግቢ መካከልም እሳት አንድደው በአንድነት ተቀምጠው ሳሉ ጴጥሮስ በመካከላቸው ተቀመጠ። ፶፮ በብርሃኑም በኩል ተቀምጦ ሳለ አንዲት ገረድ አየችውና ትኵር ብላ። ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ አለች። ፶፯ እርሱ ግን። አንቺ ሴት፥ አላውቀውም ብሎ ካደ። ፶፰ ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሌላው አይቶት። አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህ አለው። ጴጥሮስ ግን። አንተ ሰው፥ እኔ አይደለሁም አለ። ፶፱ አንድ ሰዓትም የሚያህል ቆይቶ ሌላው አስረግጦ። እርሱ የገሊላ ሰው ነውና በእውነት ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ አለ። ፷ ጴጥሮስ ግን። አንተ ሰው፥ የምትለውን አላውቅም አለ። ያን ጊዜም ገና ሲናገር ዶሮ ጮኸ። ፷፩ ጌታም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም። ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እንዳለው የጌታ ቃል ትዝ አለው። ፷፪ ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ። ፷፫ ኢየሱስንም የያዙት ሰዎች ይዘብቱበትና ይደበድቡት ነበር፤ ፷፬ ሸፍነውም ፊቱን ይመቱት ነበርና። በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር እያሉ ይጠይቁት ነበር። ፷፭ ሌላም ብዙ ነገር እየተሳደቡ በእርሱ ላይ ይናገሩ ነበር። ፷፮ በነጋም ጊዜ የሕዝቡ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች ጻፎችም ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱትና ፷፯ ክርስቶስ አንተ ነህን? ንገረን አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው። ብነግራችሁ አታምኑም፤ ፷፰ ብጠይቅም አትመልሱልኝም አትፈቱኝምም። ፷፱ ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኃይል ቀኝ ይቀመጣል። ፸ ሁላቸውም። እንግዲያስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን? አሉት። እርሱም። እኔ እንደ ሆንሁ እናንተ ትላላችሁ አላቸው። ፸፩ እነርሱም። ራሳችን ከአፉ ሰምተናልና ከእንግዲህ ወዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል? አሉ።