፲፩
፩ ኢየሱስም አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ማዘዝ በፈጸመ ጊዜ በከተሞቻቸው ሊያስተምርና ሊሰብክ ከዚያ አለፈ። ፪ ዮሐንስም በወህኒ ሳለ የክርስቶስን ሥራ ሰምቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከና። ፫ የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ? አለው። ፬ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ ፭ ዕውሮች ያያሉ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ ደንቆሮችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ ፮ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው። ፯ እነዚያም ሲሄዱ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ እንዲህም አለ። ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? ፰ ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን? እነሆ፥ ቀጭን ልብስ የለበሱ በነገሥታት ቤት አሉ። ፱ ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፥ ከነቢይም የሚበልጠውን። ፲ እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ ፲፩ ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነውና። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። ፲፪ ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፥ ግፈኞችም ይናጠቋታል። ፲፫ ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ፤ ፲፬ ልትቀበሉትስ ብትወዱ፥ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው። ፲፭ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። ፲፮ ነገር ግን ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፥ እነርሱም ባልንጀሮቻቸውን እየጠሩ። ፲፯ እንቢልታ ነፋንላችሁ ዘፈንም አልዘፈናችሁም ሙሾ አወጣንላችሁ ዋይ ዋይም አላላችሁም ይሉአቸዋል። ፲፰ ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፥ እነርሱም። ጋኔን አለበት አሉት። ፲፱ የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፥ እነርሱም። እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ይሉታል። ጥበብም በልጆችዋ ጸደቀች። ፳ በዚያን ጊዜ የሚበዙ ተአምራት የተደረገባቸውን ከተማዎች ንስሐ ስላልገቡ ሊነቅፋቸው ጀመረ እንዲህም አለ። ፳፩ ወዮልሽ ኮራዚ፤ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበርና። ፳፪ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። ፳፫ አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን፥ እስከ ዛሬ በኖረች ነበርና። ፳፬ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም አገር ይቀልላታል። ፳፭ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ። አባት ሆይ፥ የሰማይና የምድር ጌታ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ ፳፮ አዎን፥ አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና። ፳፯ ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም። ፳፰ እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ፳፱ ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ፴ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።