፲፭
፩ ወዲያውም ማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎችና ከጻፎች ከሸንጎውም ሁሉ ጋር ከተማከሩ በኋላ፥ ኢየሱስን አሳስረው ወሰዱትና ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። ፪ ጲላጦስም። አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን? ብሎ ጠየቀው። እርሱም። አንተ አልህ ብሎ መለሰለት። ፫ የካህናት አለቆችም ብዙ ያሳጡት ነበር፤ እርሱ ግን ምንም አልመለሰም። ፬ ጲላጦስም ደግሞ። አንዳች አትመልስምን? እነሆ፥ በስንት ነገር ያሳጡሃል ብሎ ጠየቀው። ፭ ኢየሱስም ከዚያ በኋላ ጲላጦስ እስኪደነቅ ድረስ ምንም አልመለሰም። ፮ በዚያም በዓል የለመኑትን አንድ እስረኛ ይፈታላቸው ነበር። ፯ በዓመፅም ነፍስ ከገደሉት ከዓመፀኞች ጋር የታሰረ በርባን የተባለ ነበረ። ፰ ሕዝቡም ወጥተው እንደ ልማዱ ያደርግላቸው ዘንድ እየጮኹ ይለምኑት ጀመር። ፱ ጲላጦስም። የአይሁድን ንጉሥ እፈታላችሁ ዘንድ ትወዳላችሁን? ብሎ መለሰላቸው፤ ፲ የካህናት አለቆች በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና። ፲፩ የካህናት አለቆች ግን በርባንን በእርሱ ፈንታ ይፈታላቸው ዘንድ ሕዝቡን አወኩአቸው። ፲፪ ጲላጦስም ዳግመኛ መልሶ። እንግዲህ የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን ላደርገው ትወዳላችሁ? አላቸው። ፲፫ እነርሱም ዳግመኛ። ስቀለው እያሉ ጮኹ። ፲፬ ጲላጦስም። ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱ ግን። ስቀለው እያሉ ጩኸት አበዙ። ፲፭ ጲላጦስም የሕዝቡን ፈቃድ ሊያደርግ ወዶ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስንም ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠ። ፲፮ ወታደሮችም ፕራይቶሪዮን ወደሚባል ግቢ ውስጥ ወሰዱት፥ ጭፍራውንም ሁሉ በአንድነት ጠሩ። ፲፯ ቀይ ልብስም አለበሱት፥ የእሾህ አክሊልም ጎንጉነው ደፉበት፤ ፲፰ የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ እጅ ይነሱት ጀመር፤ ፲፱ ራሱንም በመቃ መቱት ተፉበትም፥ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ፳ ከተዘባበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት፥ ሊሰቅሉትም ወሰዱት። ፳፩ አንድ መንገድ አላፊም የአሌክስንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት። ፳፪ ትርጓሜውም የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደተባለ ስፍራ ወሰዱት። ፳፫ ከርቤም የተቀላቀለበትን የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም። ፳፬ ሰቀሉትም፥ ልብሱንም ማን ማን እንዲወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ። ፳፭ በሰቀሉትም ጊዜ ሦስት ሰዓት ነበረ። ፳፮ የክሱ ጽሕፈትም። የአይሁድ ንጉሥ የሚል ተጽፎ ነበር። ፳፯ ከእርሱም ጋር ሁለት ወንበዶች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ። ፳፰ መጽሐፍም። ከአመፀኞች ጋር ተቆጠረ ያለው ተፈጸመ። ፳፱ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና። ዋ፥ ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራ፥ ፴ ከመስቀል ወርደህ ራስህን አድን አሉ። ፴፩ እንዲሁም የካህናት አለቆች ደግሞ ከጻፎች ጋር እርስ በርሳቸው እየተዘባበቱ። ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ ፴፪ አይተን እናምን ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ አሁን ከመስቀል ይውረድ አሉ። ከእርሱም ጋር የተሰቀሉት ይነቅፉት ነበር። ፴፫ ስድስት ሰዓትም በሆነ ጊዜ፥ እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። ፴፬ በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ። ኤሎሄ፥ ኤሎሄ፥ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? ማለት ነው። ፴፭ በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው። እነሆ፥ ኤልያስን ይጠራል አሉ። ፴፮ አንዱም ሮጦ ሆምጣጤ በሰፍነግ ሞላ በመቃም አድርጎ። ተዉ፤ ኤልያስ ሊያወርደው ይመጣ እንደ ሆነ እንይ እያለ አጠጣው። ፴፯ ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ ነፍሱንም ሰጠ። ፴፰ የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ። ፴፱ በዚያም በአንጻሩ የቆመ የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ። ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ አለ። ፵-፵፪ አሁንም በመሸ ጊዜ የሰንበት ዋዜማ የሆነ የማዘጋጀት ቀን ስለ ነበረ፥ የከበረ አማካሪ የሆነ የአርማትያስ ዮሴፍ መጣ፥ ፵፫ እርሱም ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር፤ ደፍሮም ወደ ጲላጦስ ገባና የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። ፵፬ ጲላጦስም አሁኑን እንዴት ሞተ ብሎ ተደነቀ፥ የመቶ አለቃውንም ጠርቶ ከሞተ ቆይቶአልን? ብሎ ጠየቀው፤ ፵፭ ከመቶ አለቃውም ተረድቶ በድኑን ለዮሴፍ ሰጠው። ፵፮ በፍታም ገዝቶ አውርዶም በበፍታ ከፈነው ከዓለትም በተወቀረ መቃብር አኖረው፥ በመቃብሩ ደጃፍም ድንጋይ አንከባለለ። ፵፯ መግደላዊትም ማርያም የዮሳም እናት ማርያም ወዴት እንዳኖሩት ይመለከቱ ነበር።