፩ በጉም ከሰባቱ ማኅተም አንዱን በፈታ ጊዜ አየሁ፥ ከአራቱም እንስሶች አንዱ ነጐድጓድ በሚመስል ድምፅ። መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። ፪ አየሁም፥ እነሆም፥ አምባላይ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፥ አክሊልም ተሰጠው፥ ድልም እየነሣ ወጣ ድል ለመንሣት። ፫ ሁለተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሁለተኛው እንስሳ። መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። ፬ ሌላም ዳማ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን ተሰጠው፥ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው። ፭ ሦስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሦስተኛው እንስሳ። መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። አየሁም፥ እነሆም፥ ጕራቻ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ። ፮ በአራቱም እንስሶች መካከል ድምፅ። አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፥ ዘይትንና ወይንንም አትጕዳ ሲል ሰማሁ። ፯ አራተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ የአራተኛው እንስሳ ድምፅ። መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። ፰ አየሁም፥ እነሆም፥ ሐመር ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ። ሲኦልም ተከተለው፤ በሰይፍና በራብም በሞትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው። ፱ አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ። ፲ በታላቅ ድምፅም እየጮኹ። ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ። ፲፩ ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፥ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው። ፲፪ ስድስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ አየሁ፥ ታላቅም የምድር መናወጥ ሆነ፥ ፀሐይም እንደ ማቅ ጠጕር ጥቁር ሆነ፥ ጨረቃም በሞላው እንደ ደም ሆነ፥ ፲፫ በለስም በብርቱ ነፋስ ተናውጣ ቃርያዋን ፍሬ እንደምትጥል የሰማይ ከዋክብት ወደ ምድር ወደቁ፥ ፲፬ ሰማይም እንደ መጽሐፍ ተጠቅልሎ አለፈ፥ ተራራዎችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወሰዱ። ፲፭ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ፥ ፲፮ ተራራዎችንና ዓለቶችንም። በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን፤ ፲፯ ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና፥ ማንስ ሊቆም ይችላል? አሉአቸው።