፩ ወንድሞች ሆይ፥ የልቤ በጎ ፈቃድና ስለ እስራኤል ወደ እግዚአብሔር ልመናዬ እንዲድኑ ነው። ፪ በእውቀት አይቅኑ እንጂ ለእግዚአብሔር እንዲቀኑ እመሰክርላቸዋለሁና። ፫ የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፥ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም። ፬ የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና። ፭ ሙሴ ከሕግ የሆነውን ጽድቅ የሚያደርገው ሰው በእርሱ በሕይወት እንዲኖር ጽፎአልና። ፮ ከእምነት የሆነ ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል። በልብህ። ማን ወደ ሰማይ ይወጣል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ ፯ ወይም። በልብህ። ወደ ጥልቁ ማን ይወርዳል? አትበል፤ ይህ ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው። ፰ ነገር ግን ምን ይላል? በአፍህ በልብህም ሆኖ ቃሉ ቀርቦልሃል፤ ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው። ፱ ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ፲ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና። ፲፩ መጽሐፍ። በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላልና። ፲፪ በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤ ፲፫ የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና። ፲፬ እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? ፲፭ መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ? ፲፮ ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ። ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአልና። ፲፯ እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ፲፰ ዳሩ ግን። ባይሰሙ ነው ወይ? እላለሁ። በእውነት። ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ። ፲፱ ነገር ግን። እስራኤል ባያውቁ ነው ወይ? እላለሁ። ሙሴ አስቀድሞ። እኔ ሕዝብ በማይሆነው አስቀናችኋለሁ በማያስተውልም ሕዝብ አስቆጣችኋለሁ ፳ ብሎአል። ኢሳይያስም ደፍሮ። ላልፈለጉኝ ተገኘሁ፥ ላልጠየቁኝም ተገለጥሁ አለ። ፳፩ ስለ እስራኤል ግን። ቀኑን ሁሉ ወደማይታዘዝና ወደሚቃወም ሕዝብ እጆቼን ዘረጋሁ ይላል።