፲፫
 ፩ በዚያን ጊዜም ሰዎች መጥተው ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስላደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች አወሩለት።  ፪ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ስለ ደረሰባቸው ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሉአችኋልን?  ፫ እላችኋለሁ፥ አይደለም፤ ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንዲሁ ትጠፋላችሁ።  ፬ ወይስ በሰሌሆም ግንቡ የወደቀባቸውና የገደላቸው እነዚያ አሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሁሉ ይልቅ በደለኞች ይመስሉአችኋልን? አይደለም፥ እላችኋለሁ፤  ፭ ነገር ግን ንስሐ ባትገቡ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ።  ፮ ይህንም ምሳሌ አለ። ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፥ ፍሬም ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም።  ፯ የወይን አትክልት ሠራተኛውንም። እነሆ፥ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም፤ ቍረጣት፤ ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቍላለች? አለው።  ፰ እርሱ ግን መልሶ። ጌታ ሆይ፥ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት።  ፱ ወደ ፊትም ብታፈራ፥ ደኅና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ አለው።  ፲ በሰንበትም በአንድ ምኵራብ ያስተምር ነበር።  ፲፩ እነሆም፥ ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ የድካም መንፈስ ያደረባት ሴት ነበረች፥ እርስዋም ጐባጣ ነበረች ቀንታም ልትቆም ከቶ አልተቻላትም።  ፲፪ ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና። አንቺ ሴት፥ ከድካምሽ ተፈትተሻል አላት፥ እጁንም ጫነባት፤  ፲፫ ያን ጊዜም ቀጥ አለች፥ እግዚአብሔርንም አመሰገነች።  ፲፬ የምኵራብ አለቃ ግን ኢየሱስ በሰንበት ስለ ፈወሰ ተቈጥቶ መለሰና ሕዝቡን። ሊሠራባቸው የሚገባ ስድስት ቀኖች አሉ፤ እንግዲህ በእነርሱ መጥታችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት አይደለም አለ።  ፲፭ ጌታም መልሶ። እናንተ ግብዞች፥ ከእናንተ እያንዳንዱ በሰንበት በሬውን ወይስ አህያውን ከግርግሙ ፈትቶ ውኃ ሊያጠጣው ይወስደው የለምን?  ፲፮ ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሰራት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው።  ፲፯ ይህንም ሲናገር ሳለ የተቃወሙት ሁሉ አፈሩ፤ ከእርሱም በተደረገው ድንቅ ሁሉ ሕዝቡ ሁሉ ደስ አላቸው።  ፲፰ እርሱም። የእግዚአብሔር መንግሥት ምን ትመስላለች፥ በምንስ አስመስላታለሁ?  ፲፱ ሰው ወስዶ በአትክልቱ የጣላትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ አደገችም ታላቅ ዛፍም ሆነች፥ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ ሰፈሩ አለ።  ፳ ደግሞም፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት በምን አስመስላታለሁ?  ፳፩ ሴት ወስዳ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች አለ።  ፳፪ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ከተማዎችንና መንደሮችን እያስተማረ ያልፍ ነበር።  ፳፫ አንድ ሰውም። ጌታ ሆይ፥ የሚድኑ ጥቂቶች ናቸውን? አለው። እርሱም እንዲህ አላቸው።  ፳፬ በጠበበው በር ለመግባት ተጋደሉ፤ እላችኋለሁና፥ ብዙዎች ሊገቡ ይፈልጋሉ አይችሉምም።  ፳፭ ባለቤቱ ተነሥቶ በሩን ከቈለፈ በኋላ፥ እናንተ በውጭ ቆማችሁ። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን እያላችሁ በሩን ልታንኳኩ ትጀምራላችሁ እርሱም መልሶ። ከወዴት እንደ ሆናችሁ አላውቃችሁም ይላችኋል።  ፳፮ በዚያን ጊዜም። በፊትህ በላን ጠጣንም በአደባባያችንም አስተማርህ ልትሉ ትጀምራላችሁ፤  ፳፯ እርሱም። እላችኋለሁ፥ ከወዴት እንደ ሆናችሁ አላውቃችሁም፤ ሁላችሁ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ይላችኋል።  ፳፰ አብርሃምንና ይስሐቅን ያዕቆብንም ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ባያችሁ ጊዜ፥ እናንተ ግን ወደ ውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ፥ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።  ፳፱ ከምሥራቅና ከምዕራብም ከሰሜንና ከደቡብም ይመጣሉ፥ በእግዚአብሔርም መንግሥት በማዕድ ይቀመጣሉ።  ፴ እነሆም፥ ከኋለኞች ፊተኞች የሚሆኑ አሉ፥ ከፊተኞችም ኋለኞች የሚሆኑ አሉ።  ፴፩ በዚያን ሰዓት ከፈሪሳውያን አንዳንዱ ቀርበው። ሄሮድስ ሊገድልህ ይወዳልና ከዚህ ውጣና ሂድ አሉት።  ፴፪ እንዲህም አላቸው። ሄዳችሁ ለዚያች ቀበሮ። እነሆ፥ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ በሽተኞችንም እፈውሳለሁ፥ በሦስተኛውም ቀን እፈጸማለሁ በሉአት።  ፴፫ ዳሩ ግን ነቢይ ከኢየሩሳሌም ውጭ ይጠፋ ዘንድ አይገባውምና ዛሬና ነገ ከነገ በስቲያም ልሄድ ያስፈልገኛል።  ፴፬ ኢየሩሳሌም፥ ኢየሩሳሌም፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ፥ እናንተም አልወደዳችሁም።  ፴፭ እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል። እላችኋለሁም፥ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።