፲፬
 ፩ በሰንበትም ከፈሪሳውያን አለቆች ወደ አንዱ ቤት እንጀራ ሊበላ በገባ ጊዜ እነርሱ ይጠባበቁት ነበር።  ፪ እነሆም፥ ሆዱ የተነፋ ሰው በፊቱ ነበረ።  ፫ ኢየሱስም መልሶ። በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? ብሎ ለሕግ አዋቂዎችና ለፈሪሳውያን ተናገረ።  ፬ እነርሱ ግን ዝም አሉ። ይዞም ፈወሰውና አሰናበተው።  ፭ ከእናንተ አህያው ወይስ በሬው በጕድጓድ ቢወድቅ በሰንበት ወዲያው የማያወጣው ማን ነው? አላቸው።  ፮ ስለዚህ ነገርም ሊመልሱለት አልተቻላቸውም።  ፯ የታደሙትንም የከበሬታ ስፍራ እንደ መረጡ ተመልክቶ ምሳሌ ነገራቸው እንዲህ ሲል።  ፰ ማንም ለሰርግ ቢጠራህ በከበሬታ ስፍራ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ ይልቅ የከበረ ተጠርቶ ይሆናልና አንተን እርሱንም የጠራ መጥቶ።  ፱ ለዚህ ስፍራ ተውለት ይልሃል፥ በዚያን ጊዜም እያፈርህ በዝቅተኛው ስፍራ ልትሆን ትጀምራለህ።  ፲ ነገር ግን በተጠራህ ጊዜ፥ የጠራህ መጥቶ። ወዳጄ ሆይ፥ ወደ ላይ ውጣ እንዲልህ፥ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ ያን ጊዜም ከአንተ ጋር በተቀመጡት ሁሉ ፊት ክብር ይሆንልሃል።  ፲፩ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል።  ፲፪ የጠራውንም ደግሞ እንዲህ አለው። ምሳ ወይም እራት ባደረግህ ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ በተራቸው ምናልባት እንዳይጠሩህ ብድራትም እንዳይመልሱልህ፥ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን ዘመዶችህንም ባለ ጠጎች ጎረቤቶችህንም አትጥራ።  ፲፫ ነገር ግን ግብዣ ባደረግህ ጊዜ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንም ዕውሮችንም ጥራ፤  ፲፬ የሚመልሱት ብድራት የላቸውምና ብፁዕ ትሆናለህ፤ በጻድቃን ትንሣኤ ይመለስልሃልና።  ፲፭ ከተቀመጡትም አንዱ ይህን ሰምቶ። በእግዚአብሔር መንግሥት እንጀራ የሚበላ ብፁዕ ነው አለው።  ፲፮ እርሱ ግን እንዲህ አለው። አንድ ሰው ታላቅ እራት አድርጎ ብዙዎችን ጠራ፤  ፲፯ በእራትም ሰዓት የታደሙትን። አሁን ተዘጋጅቶአልና ኑ እንዲላቸው ባሪያውን ላከ።  ፲፰ ሁላቸውም በአንድነት ያመካኙ ጀመር። የፊተኛው። መሬት ገዝቼአለሁ ወጥቼም ላየው በግድ ያስፈልገኛል፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው።  ፲፱ ሌላውም። አምስት ጥምድ በሬዎች ገዝቼአለሁ ልፈትናቸውም እሄዳለሁ፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው።  ፳ ሌላውም። ሚስት አግብቼአለሁ ስለዚህም ልመጣ አልችልም አለው።  ፳፩ ባሪያውም ደርሶ ይህን ለጌታው ነገረው። በዚያን ጊዜ ባለቤቱ ተቆጥቶ ባሪያውን። ወደ ከተማ ጎዳናና ወደ ስላች ፈጥነህ ውጣ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንና ዕውሮችንም ወደዚህ አግባ አለው።  ፳፪ ባሪያውም። ጌታ ሆይ፥ እንዳዘዝኸኝ ተደርጎአል፥ ገናም ስፍራ አለ አለው።  ፳፫ ጌታውም ባሪያውን። ቤቴ እንዲሞላ ወደ መንገድና ወደ ቅጥር ውጣና ይገቡ ዘንድ ግድ በላቸው፤  ፳፬ እላችኋለሁና፥ ከታደሙት ከእነዚያ ሰዎች አንድ ስንኳ እራቴን አይቀምስም አለው።  ፳፭ ብዙም ሕዝብ ከእርሱ ጋር ይሄዱ ነበር፥ ዘወር ብሎም እንዲህ አላቸው።  ፳፮ ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።  ፳፯ ማንም መስቀሉን ተሸክሞ በኋላዬ የማይመጣ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።  ፳፰ ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ከሳራውን የማይቈጥር ማን ነው?  ፳፱ ያለዚያ መሠረቱን ቢመሠርት፥ ሊደመድመውም ቢያቅተው፥ ያዩት ሁሉ።  ፴ ይህ ሰው ሊሠራ ጀምሮ ሊደመድመው አቃተው ብለው ሊዘብቱበት ይጀምራሉ።  ፴፩ ወይም ሌላውን ንጉሥ በጦርነት ሊጋጠም የሚሄድ፥ ከሁለት እልፍ ጋር የሚመጣበትን በአንድ እልፍ ሊገናኝ የሚችል እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ የማያስብ ንጉሥ ማን ነው?  ፴፪ ባይሆንስ ሌላው ገና ሩቅ ሳለ መልክተኞች ልኮ ዕርቅ ይለምናል።  ፴፫ እንግዲህ እንደዚሁ ማንም ከእናንተ ያለውን ሁሉ የማይተው ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።  ፴፬ ጨው መልካም ነው፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፈጣል?  ፴፭ ለምድር ቢሆን ለፍግ መቈለያም ቢሆን አይረባም፤ ወደ ውጭ ይጥሉታል። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።