፲፯
 ፩ ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ። መሰናክል ግድ ሳይመጣ አይቀርም፥ ነገር ግን መሰናክሉን ለሚያመጣው ወዮለት፤  ፪ ከእነዚህ ከታናናሾች አንዱን ከማሰናከል ይልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይጠቅመው ነበር።  ፫ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። ወንድምህ ቢበድልህ ገሥጸው፥ ቢጸጸትም ይቅር በለው።  ፬ በቀንም ሰባት ጊዜ እንኳ ቢበድልህ በቀንም ሰባት ጊዜ። ተጸጸትሁ እያለ ወደ አንተ ቢመለስ፥ ይቅር በለው።  ፭ ሐዋርያትም ጌታን። እምነት ጨምርልን አሉት።  ፮ ጌታም አለ። የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት፥ ይታዘዝላችሁ ነበር።  ፯ ከእናንተም የሚያርስ ወይም ከብትን የሚጠብቅ ባሪያ ያለው፥ ከእርሻ ሲመለስ። ወዲያው ቅረብና በማዕድ ተቀመጥ የሚለው ማን ነው?  ፰ የምበላውን እራቴን አሰናዳልኝ፥ እስክበላና እስክጠጣ ድረስ ታጥቀህ አገልግለኝ፥ በኋላም አንተ ብላና ጠጣ የሚለው አይደለምን?  ፱ ያንን ባሪያ ያዘዘውን ስላደረገ ያመሰግነዋልን?  ፲ እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ። የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፥ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ።  ፲፩ ወደ ኢየሩሳሌምም ሲሄድ በገሊላና በሰማርያ መካከል አለፈ።  ፲፪ ወደ አንዲት መንደርም ሲገባ በሩቅ የቆሙት አሥር ለምጻሞች ተገናኙት፤  ፲፫ እነርሱም እየጮኹ። ኢየሱስ ሆይ፥ አቤቱ፥ ማረን አሉ።  ፲፬ አይቶም። ሂዱ፥ ራሳችሁን ለካህናት አሳዩ አላቸው።  ፲፭ እነሆም፥ ሲሄዱ ነጹ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፥  ፲፮ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ።  ፲፯ ኢየሱስም መልሶ። አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ?  ፲፰ ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ።  ፲፱ እርሱንም። ተነሣና ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው።  ፳ ፈሪሳውያንም። የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ። የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤  ፳፩ ደግሞም። እንኋት በዚህ ወይም። እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው።  ፳፪ ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ። ከሰው ልጅ ቀኖች አንዱን ልታዩ የምትመኙበት ወራት ይመጣል አታዩትምም።  ፳፫ እነርሱም። እነሆ በዚህ፥ ወይም። እነሆ በዚያ ይሉአችኋል፤ አትሂዱ አትከተሉአቸውም።  ፳፬ መብረቅ በርቆ ከሰማይ በታች ካለ ከአንድ አገር ከሰማይ በታች ወዳለው ወደ ሌላ አገር እንደሚያበራ፥ የሰው ልጅ በቀኑ እንዲህ ይሆናል።  ፳፭ አስቀድሞ ግን ብዙ መከራ እንዲቀበል ከዚህም ትውልድ እንዲጣል ይገባዋል።  ፳፮ በኖኅ ዘመንም እንደ ሆነ፥ በሰው ልጅ ዘመን ደግሞ እንዲሁ ይሆናል።  ፳፯ ኖኅ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ፥ ይበሉና ይጠጡ ያገቡና ይጋቡም ነበር፥ የጥፋት ውኃም መጣ ሁሉንም አጠፋ።  ፳፰ እንዲሁ በሎጥ ዘመን እንደ ሆነ፤ ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተክሉም ቤትም ይሠሩ ነበር፤  ፳፱ ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ ሁሉንም አጠፋ።  ፴ የሰው ልጅ በሚገለጥበት ቀን እንዲሁ ይሆናል።  ፴፩ በዚያም ቀን በሰገነት ያለ በቤቱ ያለውን ዕቃ ሊወስድ አይውረድ፥ እንዲሁም በእርሻ ያለ ወደ ኋላው አይመለስ።  ፴፪ የሎጥን ሚስት አስቡአት።  ፴፫ ነፍሱን ሊያድን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም የሚያጠፋ ሁሉ በሕይወት ይጠብቃታል።  ፴፬ እላችኋለሁ፥ በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ አልጋ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሁለተኛውም ይቀራል።  ፴፭ ሁለት ሴቶች በአንድ ወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች ሁለተኛይቱም ትቀራለች።  ፴፮ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል ሁለተኛውም ይቀራል።  ፴፯ መልሰውም። ጌታ ሆይ፥ ወዴት ነው? አሉት። እርሱም። ሥጋ ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ አላቸው።