፲፰
 ፩ ሳይታክቱም ዘወትር ሊጸልዩ እንዲገባቸው የሚል ምሳሌን ነገራቸው፥  ፪ እንዲህ ሲል። በአንዲት ከተማ እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰውንም የማያፍር አንድ ዳኛ ነበረ።  ፫ በዚያችም ከተማ አንዲት መበለት ነበረች፥ ወደ እርሱም እየመጣች። ከባላጋራዬ ፍረድልኝ ትለው ነበር።  ፬ አያሌ ቀንም አልወደደም፤ ከዚህ በኋላ ግን በልቡ። ምንም እግዚአብሔርን ባልፈራ ሰውንም ባላፍር፥  ፭ ይህች መበለት ስለምታደክመኝ ሁልጊዜም እየመጣች እንዳታውከኝ እፈርድላታለሁ አለ።  ፮ ጌታም አለ። ዓመፀኛው ዳኛ ያለውን ስሙ።  ፯ እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን?  ፰ እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?  ፱ ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፥  ፲ እንዲህ ሲል። ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፥ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ።  ፲፩ ፈሪሳዊም ቆሞ በልቡ ይህን ሲጸልይ። እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤  ፲፪ በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፥ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት አወጣለሁ አለ።  ፲፫ ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን። አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር።  ፲፬ እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል።  ፲፭ እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ደግሞ ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም አይተው ገሠጹአቸው።  ፲፮ ኢየሱስ ግን ሕፃናትን ወደ እርሱ ጠርቶ። ሕፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉአቸው አትከልክሉአቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና።  ፲፯ እውነት እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም አለ።  ፲፰ ከአለቆችም አንዱ። ቸር መምህር፥ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው።  ፲፱ ኢየሱስም። ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም።  ፳ ትእዛዛቱን ታውቃለህ፥ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው።  ፳፩ እርሱም። ይህን ሁሉ ከሕፃንናቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ አለ።  ፳፪ ኢየሱስም ይህን ሰምቶ። አንዲት ገና ቀርታሃለች፤ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ አለው።  ፳፫ እርሱ ግን ይህን ሰምቶ እጅግ ባለ ጠጋ ነበርና ብዙ አዘነ።  ፳፬ ኢየሱስም ብዙ እንዳዘነ አይቶ። ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል።  ፳፭ ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ሊገባ ይቀላል አለ።  ፳፮ የሰሙትም። እንግዲህ ማን ሊድን ይችላል? አሉ።  ፳፯ እርሱ ግን። በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል አለ።  ፳፰ ጴጥሮስም። እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ አለ።  ፳፱ እርሱም። እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ቤትን ወይም ወላጆችን ወይም ወንድሞችን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን የተወ፥  ፴ በዚህ ዘመን ብዙ እጥፍ በሚመጣውም ዓለም የዘላለምን ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም አላቸው።  ፴፩ አሥራ ሁለቱንም ወደ እርሱ አቅርቦ እንዲህ አላቸው። እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ ስለ ሰው ልጅም በነቢያት የተጻፈው ሁሉ ይፈጸማል።  ፴፪ ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታልና፥ ይዘብቱበትማል ያንገላቱትማል ይተፉበትማል፤  ፴፫ ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል።  ፴፬ እነርሱም ከዚህ ነገር ምንም አላስተዋሉም፥ ይህም ቃል ተሰውሮባቸው ነበር፥ የተናገረውንም አላወቁም።  ፴፭ ወደ ኢያሪኮም በቀረበ ጊዜ አንድ ዕውር እየለመነ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ነበር።  ፴፮ ሕዝብም ሲያልፍ ሰምቶ። ይህ ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀ።  ፴፯ እነርሱም። የናዝሬቱ ኢየሱስ ያልፋል ብለው አወሩለት።  ፴፰ እርሱም። የዳዊት ልጅ፥ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ እያለ ጮኸ።  ፴፱ በስተ ፊት ይሄዱ የነበሩትም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን። የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ እያለ አብዝቶ ጮኸ።  ፵ ኢየሱስም ቆሞ ወደ እርሱ እንዲያመጡት አዘዘ። በቀረበም ጊዜ። ምን ላደርግልህ ትወዳለህ? ብሎ ጠየቀው።  ፵፩ እርሱም። ጌታ ሆይ፥ አይ ዘንድ ነው አለው።  ፵፪ ኢየሱስም። እይ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው።  ፵፫ በዚያን ጊዜም አየ፥ እግዚአብሔንም እያከበረ ተከተለው። ሕዝቡም ሁሉ አይተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ።