፲፱
 ፩-፫ ኢየሱስንም የትኛው እንደ ሆነ ሊያይ ይፈልግ ነበር፤ ቁመቱም አጭር ነበረና ስለ ሕዝቡ ብዛት አቃተው።  ፬ በዚያችም መንገድ ያልፍ ዘንድ አለውና ያየው ዘንድ ወደ ፊት ሮጦ በአንድ ሾላ ላይ ወጣ።  ፭ ኢየሱስም ወደዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ፥ አሻቅቦ አየና። ዘኬዎስ ሆይ፥ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ አለው።  ፮ ፈጥኖም ወረደ በደስታም ተቀበለው።  ፯ ሁሉም አይተው። ከኃጢአተኛ ሰው ጋር ሊውል ገባ ብለው አንጐራጐሩ።  ፰ ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን። ጌታ ሆይ፥ ካለኝ ሁሉ እኵሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደ ሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ አለው።  ፱ ኢየሱስም። እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል፤  ፲ የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና አለው።  ፲፩ እነርሱም ይህን ሲሰሙ፥ ወደ ኢየሩሳሌም መቅረቡ ስለ ሆነ የእግዚአብሔርም መንግሥት ፈጥኖ ሊገለጥ እንዳለው ስለ መሰላቸው ምሳሌ ጭምር ተናገረ።  ፲፪ ስለዚህም እንዲህ አላቸው። አንድ መኰንን ለራሱ መንግሥትን ይዞ ሊመለሰ ወደ ሩቅ አገር ሄደ።  ፲፫ አሥር ባሪያዎችንም ጠርቶ አሥር ምናን ሰጣቸውና። እስክመጣ ድረስ ነግዱ አላቸው።  ፲፬ የአገሩ ሰዎች ግን ይጠሉት ነበርና። ይህ በላያችን ሊነግሥ አንወድም ብለው በኋላው መልክተኞችን ላኩ።  ፲፭ መንግሥትንም ይዞ በተመለሰ ጊዜ፥ ገንዘብ የሰጣቸውን እነዚህን ባሪያዎች ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ያውቅ ዘንድ እንዲጠሩለት አዘዘ።  ፲፮ የፊተኛውም ደርሶ። ጌታ ሆይ፥ ምናንህ አሥር ምናን አተረፈ አለው።  ፲፯ እርሱም። መልካም፥ አንተ በጎ ባሪያ፥ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በአሥር ከተማዎች ላይ ሥልጣን ይሁንልህ አለው።  ፲፰ ሁለተኛውም መጥቶ። ጌታ ሆይ፥ ምናንህ አምስት ምናን አተረፈ አለው።  ፲፱ ይህንም ደግሞ። አንተም በአምስት ከተማዎች ላይ ሁን አለው።  ፳ ሌላውም መጥቶ። ጌታ ሆይ፥ በጨርቅ ጠቅልዬ የጠበቅኋት ምናንህ እነሆ፤  ፳፩ ፈርቼሃለሁና፥ ጨካኝ ሰው ስለ ሆንህ፤ ያላኖርኸውን ትወስዳለህ ያልዘራኸውንም ታጭዳለህ አለው።  ፳፪ እርሱም። አንተ ክፉ ባሪያ፥ አፍህ በተናገረው እፈርድብሃለሁ። እኔ ያላኖርሁትን የምወስድና ያልዘራሁትን የማጭድ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ አወቅህ፤ ምን ነው ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ያልሰጠኸው?  ፳፫ እኔም መጥቼ ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር አለው።  ፳፬ በዚያም ቆመው የነበሩትን። ምናኑን ውሰዱበት አሥሩ ምናን ላለውም ስጡት አላቸው።  ፳፭ እነርሱም። ጌታ ሆይ፥ አሥር ምናን አለው አሉት።  ፳፮ እላችኋለሁ፥ ላለው ሁሉ ይሰጠዋል፥ ከሌለው ግን ያው ያለው ስንኳ ይወሰድበታል።  ፳፯ ነገር ግን እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡአቸው በፊቴም እረዱአቸው።  ፳፰ ይህንም ከተናገረ በኋላ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ይቀድማቸው ነበር።  ፳፱ ደብረ ዘይትም በሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከና።  ፴ በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ ወደ እርስዋም ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፥ ፈትታችሁም አምጡት።  ፴፩ ማንም። ስለ ምን ትፈቱታላችሁ? ብሎ ቢጠይቃችሁ፥ እንዲሁ። ለጌታ ያስፈልገዋል በሉ አላቸው።  ፴፪ የተላኩትም ሄደው እንዳላቸው አገኙ።  ፴፫ እነርሱም ውርንጫውን ሲፈቱ ጌቶቹ። ውርንጫውን ስለ ምን ትፈቱታላችሁ? አሉአቸውም  ፴፬ እነርሱም። ለጌታ ያስፈልገዋል አሉ።  ፴፭ ወደ ኢየሱስም አመጡት፥ በውርንጫውም ላይ ልብሳቸውን ጭነው ኢየሱስን አስቀመጡት።  ፴፮ ሲሄድም ልብሳቸውን በመንገድ ያነጥፉ ነበር።  ፴፯ ወደ ደብረ ዘይት ቍልቍለትም አሁን በቀረበ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ሁላቸው ደስ እያላቸው ተአምራትን ሁሉ ስላዩ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን ሊያመሰግኑ ጀምረው።  ፴፰ በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው፤ በሰማይ ሰላም በአርያምም ክብር አሉ።  ፴፱ ከሕዝብም መካከል ከፈሪሳውያን አንዳንዱ። መምህር ሆይ፥ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት።  ፵ መልሶም። እላችኋለሁ፥ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ አላቸው።  ፵፩ ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፥  ፵፪ እንዲህ እያለ። ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል።  ፵፫ ወራት ይመጣብሻልና፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤  ፵፬ አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና።  ፵፭ ወደ መቅደስም ገብቶ በእርሱ የሚሸጡትን የሚገዙትንም ያወጣ ጀመር፤  ፵፮ እርሱም። ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት አላቸው።  ፵፯ ዕለት ዕለትም በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች የሕዝቡ ታላላቆችም ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፥  ፵፰ የሚያደርጉበትንም አጡ፤ ሕዝቡ ሁሉ ሲሰሙት ተንጠልጥለውበት ነበርና።