፲፮
 ፩ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንም ቀርበው ሲፈትኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ለመኑት።  ፪ እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው። በመሸ ጊዜ። ሰማዩ ቀልቶአልና ብራ ይሆናል ትላላችሁ፤  ፫ ማለዳም። ሰማዩ ደምኖ ቀልቶአልና ዛሬ ይዘንባል ትላላችሁ። የሰማዩን ፊትማ መለየት ታውቃላችሁ፥ የዘመኑንስ ምልክት መለየት አትችሉምን?  ፬ ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ትቶአቸውም ሄደ።  ፭ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ማዶ በመጡ ጊዜ እንጀራ መያዝን ረሱ።  ፮ ኢየሱስም። ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ አላቸው።  ፯ እነርሱም። እንጀራ ባንይዝ ነው ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።  ፰ ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው። እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እንጀራ ስለ ሌላችሁ ስለ ምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? ገና አታስተውሉምን?  ፱ ለአምስቱ ሺህ አምስቱ እንጀራ፥ ስንት መሶብም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን?  ፲ ወይስ ለአራቱ ሺህ ሰባቱ እንጀራ፥ ስንት ቅርጫትም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን?  ፲፩ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ እንድትጠበቁ ብዬ ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉምን?  ፲፪ እነርሱም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠበቁ እንዳላላቸው ያን ጊዜ አስተዋሉ።  ፲፫ ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን። ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ።  ፲፬ እነርሱም። አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት።  ፲፭ እርሱም። እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው።  ፲፮ ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ። አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ።  ፲፯ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።  ፲፰ እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።  ፲፱ የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።  ፳ ያን ጊዜም እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለማንም እንዳይነግሩ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው።  ፳፩ ከዚያን ቀን ጀምሮ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጥላቸው ጀመር።  ፳፪ ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ። አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገሥጸው ጀመረ።  ፳፫ እርሱ ግን ዘወር ብሎ ጴጥሮስን። ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው።  ፳፬ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ። እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።  ፳፭ ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል።  ፳፮ ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?  ፳፯ የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል።  ፳፰ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።