፲፯
 ፩ ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው።  ፪ በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ።  ፫ እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።  ፬ ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ።  ፭ እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።  ፮ ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር።  ፯ ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና። ተነሡ አትፍሩም አላቸው።  ፰ ዓይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም።  ፱ ከተራራውም በወረዱ ጊዜ ኢየሱስ። የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው።  ፲ ደቀ መዛሙርቱም። እንግዲህ ጻፎች። ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ ይገባዋል ስለ ምን ይላሉ? ብለው ጠየቁት።  ፲፩ ኢየሱስም መልሶ። ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናል፤  ፲፪ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ኤልያስ ከዚህ በፊት መጣ፤ የወደዱትንም ሁሉ አደረጉበት እንጂ አላወቁትም፤ እንዲሁም ደግሞ የሰው ልጅ ከእነርሱ መከራ ይቀበል ዘንድ አለው አላቸው።  ፲፫ በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለ መጥምቁ ስለ ዮሐንስ እንደ ነገራቸው አስተዋሉ።  ፲፬ ወደ ሕዝቡም ሲደርሱ አንድ ሰው ወደ እርሱ ቀረበና ተንበርክኮ። ጌታ ሆይ፥ ልጄን ማርልኝ፥ በጨረቃ እየተነሣበት ክፉኛ ይሣቀያልና፤  ፲፭ ብዙ ጊዜ በእሳት ብዙ ጊዜም በውኃ ይወድቃልና።  ፲፮ ወደ ደቀ መዛሙርትህም አመጣሁት ሊፈውሱትም አቃታቸው አለው።  ፲፯ ኢየሱስም መልሶ። የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደዚህ ወደ እኔ አምጡት አለ።  ፲፰ ኢየሱስም ገሠጸው ጋኔኑም ከእርሱ ወጣ፥ ብላቴናውም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰ።  ፲፱ ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀረቡና። እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምን ነው? አሉት።  ፳ ኢየሱስም። ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ። ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም።  ፳፩ ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጦም በቀር አይወጣም አላቸው።  ፳፪ በገሊላም ሲመላለሱ ኢየሱስ። የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው፥ ይገድሉትማል፥  ፳፫ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው። እጅግም አዘኑ።  ፳፬ ወደ ቅፍርናሆምም በመጡ ጊዜ ግብር የሚቀበሉ ሰዎች ወደ ጴጥሮስ ቀረቡና። መምህራችሁ ሁለቱን ዲናር*ፍ1* አይገብርምን? አሉት።  ፳፭ አዎን ይገብራል አለ። ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ኢየሱስ አስቀድሞ። ስምዖን ሆይ፥ ምን ይመስልሃል? የምድር ነገሥታት ቀረጥና ግብር ከማን ይቀበላሉ? ከልጆቻቸውን ወይስ ከእንግዶች? አለው።  ፳፮ ጴጥሮስም። ከእንግዶች ባለው ጊዜ ኢየሱስ። እንኪያስ ልጆቻቸው ነጻ ናቸው።  ፳፯ ነገር ግን እንዳናሰናክላቸው፥ ወደ ባሕር ሂድና መቃጥን ጣል፥ መጀመሪያም የሚወጣውን ዓሣ ውሰድና አፉን ስትከፍት እስታቴር*ፍ2* ታገኛለህ፤ ያን ወስደህ ስለ እኔና ስለ አንተ ስጣቸው አለው።