፪
 ፩ ስለዚህ፥ አንተ የምትፈርድ ሰው ሁሉ ሆይ፥ የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው በምትፈርድበት ነገር ራስህን ትኰንናለህና፤ አንተው ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና።  ፪ እንደዚህም በሚያደርጉት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እንደ ሆነ እናውቃለን።  ፫ አንተም እንደዚህ በሚያደርጉ የምትፈርድ ያንም የምታደርግ ሰው ሆይ፥ አንተ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን?  ፬ ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን?  ፭ ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ።  ፮ እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል፤  ፯ በበጎ ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤  ፰ ለዓመፃ በሚታዘዙ እንጂ ለእውነት በማይታዘዙትና በአድመኞች ላይ ግን ቍጣና መቅሠፍት ይሆንባቸዋል።  ፱ ክፉውን በሚያደርግ ሰው ነፍስ ሁሉ መከራና ጭንቀት ይሆንበታል፥ አስቀድሞ በአይሁዳዊ ደግሞም በግሪክ ሰው፤  ፲ ነገር ግን በጎ ሥራ ለሚያደርጉ ሁሉ ምስጋናና ክብር ሰላምም ይሆንላቸዋል፥ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው።  ፲፩ እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላምና።  ፲፪ ያለ ሕግ ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ ያለ ሕግ ደግሞ ይጠፋሉና፤ ሕግም ሳላቸው ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል፤  ፲፫ በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉት ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ ጻድቃን አይደሉምና።  ፲፬ ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ፥ እነዚያ ሕግ ባይኖራቸው እንኳ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና፤  ፲፭ እነርሱም ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፥ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ።  ፲፮ ይህም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ እኔ በወንጌል እንዳስተማርሁ በሰው ዘንድ የተሰወረውን በሚፈርድበት ቀን ይሆናል።  ፲፯ አንተ ግን አይሁዳዊ ብትባል በሕግም ብትደገፍ በእግዚአብሔርም ብትመካ፥  ፲፰ ፈቃዱንም ብታውቅ ከሕግም ተምረህ የሚሻለውን ፈትነህ ብትወድ፤  ፲፱-፳፩ እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን?  ፳፪ አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህን?  ፳፫ በሕግ የምትመካ ሕግን በመተላለፍ እግዚአብሔርን ታሳፍራለህን?  ፳፬ በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደ ተጻፈ።  ፳፭ ሕግን ብታደርግ መገረዝስ ይጠቅማል፤ ሕግን ተላላፊ ብትሆን ግን መገረዝህ አለ መገረዝ ሆኖአል።  ፳፮ እንግዲህ ያልተገረዘ ሰው የሕግን ሥርዓት ቢጠብቅ አለመገረዙ እንደ መገረዝ ሆኖ አይቈጠርለትምን?  ፳፯ ከፍጥረቱም ያልተገረዘ ሕግን የሚፈጽም ሰው የሕግ መጽሐፍና መገረዝ ሳለህ ሕግን በምትተላለፈው በአንተ ይፈርድብሃል።  ፳፰ በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፥ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤  ፳፱ ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፥ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም፤ የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም።