፫
 ፩ እንግዲህ የአይሁዳዊ ብልጫው ምንድር ነው? ወይስ የመገረዝ ጥቅሙ ምንድር ነው? በሁሉ ነገር ብዙ ነው።  ፪ አስቀድሞ የእግዚአብሔር ቃላት አደራ ተሰጡአቸው። ታዲያ ምንድር ነው?  ፫ የማያምኑ ቢኖሩ አለማመናቸው የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያስቀራልን?  ፬ እንዲህ አይሁን፤ በቃልህ ትጸድቅ ዘንድ ወደ ፍርድ በገባህም ጊዜ ትረታ ዘንድ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ሰው ሁሉ ውሸተኛ ከሆነ እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን።  ፭ ነገር ግን ዓመፃችን የእግዚአብሔርን ጽድቅ የሚያስረዳ ከሆነ ምን እንላለን? ቍጣን የሚያመጣ እግዚአብሔር ዓመፀኛ ነውን? እንደ ሰው ልማድ እላለሁ።  ፮ እንዲህ አይሁን፤ እንዲህ ቢሆን እግዚአብሔር በዓለም እንዴት ይፈርዳል?  ፯ በእኔ ውሸት ግን የእግዚአብሔር እውነት ለክብሩ ከላቀ ስለምን በእኔ ደግሞ እንደ ኃጢአተኛ ገና ይፈርድብኛል?  ፰ ስለ ምንስ መልካም እንዲመጣ ክፉ አናደርግም? እንዲሁ ይሰድቡናልና አንዳንዱም እንዲሁ እንድንል ይናገራሉና። የእነርሱም ፍርድ ቅን ነው።  ፱ እንግዲህ ምን ይሁን? ከእነርሱ እንበልጣለንን? ከቶ አይደለም፤ አይሁድም የግሪክ ሰዎችም ሁሉ ከኃጢአት በታች እንደ ሆኑ አስቀድመን ከሰናቸዋልና፤  ፲ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ።  ፲፩ ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥  ፲፪ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም።  ፲፫ ጕሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፥ በመላሳቸውም ሸንግለዋል፤ የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፤  ፲፬ አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል፤  ፲፭ እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው፤  ፲፮ ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ይገኛል፥  ፲፯-፲፱ አፍም ሁሉ ይዘጋ ዘንድ ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ይሆን ዘንድ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንዲናገር እናውቃለን፤  ፳ ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና።  ፳፩ አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥  ፳፪ እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤  ፳፫ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤  ፳፬ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ።  ፳፭ እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥  ፳፮ ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው።  ፳፯ ትምክህት እንግዲህ ወዴት ነው? እርሱ ቀርቶአል። በየትኛው ሕግ ነው? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም፥ በእምነት ሕግ ነው እንጂ።  ፳፰ ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቆጥራለንና።  ፳፱-፴፩ እንግዲህ ሕግን በእምነት እንሽራለንን? አይደለም፤ ሕግን እናጸናለን እንጂ።