የማቴዎስ ወንጌል
፩የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ። ፪አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤ ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብም ይሁዳንና ወንድሞቹን ወለደ፤ ፫ይሁዳም ከትዕማር ፋሬስንና ዛራን ወለደ፤ ፋሬስም ኤስሮምን ወለደ፤ ፬ኤስሮምም አራምን ወለደ፤ አራምም አሚናዳብን ወለደ፤ አሚናዳብም ነአሶንን ወለደ፤ ነአሶንም ሰልሞንን ወለደ፤ ፭ሰልሞንም ከራኬብ ቦኤዝን ወለደ፤ ቦኤዝም ከሩት ኢዮቤድን ወለደ፤ ኢዮቤድም እሴይን ወለደ፤ ፮እሴይም ንጉሥ ዳዊትን ወለደ። ፯ሰሎሞንም ሮብዓምን ወለደ፤ ሮብዓምም አቢያን ወለደ፤ አቢያም አሣፍን ወለደ፤ ፰አሣፍም ኢዮሣፍጥን ወለደ፤ ኢዮሣፍጥም ኢዮራምን ወለደ፤ ኢዮራምም ዖዝያንን ወለደ፤ ፱ዖዝያንም ኢዮአታምን ወለደ፤ ኢዮአታምም አካዝን ወለደ፤ ፲አካዝም ሕዝቅያስን ወለደ፤ ሕዝቅያስም ምናሴን ወለደ፤ ምናሴም አሞፅን ወለደ፤ ፲፩አሞፅም ኢዮስያስን ወለደ፤ ኢዮስያስም በባቢሎን ምርኮ ጊዜ ኢኮንያንንና ወንድሞቹን ወለደ። ፲፪ከባቢሎንም ምርኮ በኋላ ኢኮንያን ሰላትያልን ወለደ፤ ሰላትያልም ዘሩባቤልን ወለደ፤ ፲፫ዘሩባቤልም አብዩድን ወለደ፤ አብዩድም ኤልያቄምን ወለደ፤ ኤልያቄምም አዛርን ወለደ፤ ፲፬አዛርም ሳዶቅን ወለደ፤ ሳዶቅም አኪምን ወለደ፤ አኪምም ኤልዩድን ወለደ፤ ፲፭ኤልዩድም አልዓዛርን ወለደ፤ አልዓዛርም ማታንን ወለደ፤ ማታንም ያዕቆብን ወለደ፤ ፲፮ያዕቆብም ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን የወለደች የማርያምን እጮኛ ዮሴፍን ወለደ። ፲፯እንግዲህ ትውልድ ሁሉ ከአብርሃም እስከ ዳዊት አሥራ አራት ትውልድ፥ ከዳዊትም እስከ ባቢሎን ምርኮ አሥራ አራት ትውልድ፥ ከባቢሎንም ምርኮ እስከ ክርስቶስ አሥራ አራት ትውልድ ነው። ፲፰የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። ፲፱እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ። ፳እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ። የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ፳፩ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። ፳፪በነቢይ ከጌታ ዘንድ። ፳፫እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው። ፳፬ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤ ፳፭የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም ኢየሱስ አለው።