፩ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ፤ ፪ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሉአቸዋል በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል። ፫ገንዘብንም በመመኘት በተፈጠረ ነገር ይረቡባችኋል፤ ፍርዳቸውም ከጥንት ጀምሮ አይዘገይም ጥፋታቸውም አያንቀላፋም። ፬እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ ከሰጣቸው፥ ፭ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ፥ ፮ኃጢአትንም ያደርጉ ዘንድ ላሉት ምሳሌ አድርጎ ከተማዎችን ሰዶምንና ገሞራን አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎና ገልብጦ ከፈረደባቸው፥ ፯-፲፩ዳሩ ግን መላእክት በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብን ፍርድ አያመጡም። ፲፪እነዚህ ግን ለመጠመድና ለመጥፋት በፍጥረታቸው እንደ ተወለዱ አእምሮ እንደ ሌላቸው እንስሶች ሆነው፥ በማያውቁት ነገር እየተሳደቡ በጥፋታቸው ይጠፋሉ፤ ፲፫የዓመፃቸውን ደመወዝ ይቀበላሉ። በቀን ሲዘፍኑ እንደ ተድላ ይቆጥሩታል፤ ነውረኞችና ርኵሳን ሆነው ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣ ይዘፍናሉ፤ ፲፬ምንዝር የሞላባቸው ኃጢአትንም የማይተዉ ዓይኖች አሉአቸው፤ የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፤ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው። ፲፭ቅንን መንገድ ትተው ተሳሳቱ፤ የባሶርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከተሉ፤ እርሱ የዓመፃን ደመወዝ ወደደ፥ ፲፮ነገር ግን ስለ መተላለፉ ተዘለፈ፤ ቃል የሌለው አህያ በሰው ቃል ተናግሮ የነቢዩን እብድነት አገደ። ፲፯ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው እነዚህ ውኃ የሌለባቸው ምንጮች በዐውሎ ነፋስም የተነዱ ደመናዎች ናቸው። ፲፰ከንቱና ከመጠን ይልቅ ታላቅ የሆነውን ቃል ይናገራሉና፥ በስሕተትም ከሚኖሩት አሁን የሚያመልጡትን በሥጋ ሴሰኛ ምኞት ያታልላሉ። ፲፱ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው። አርነት ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል፤ ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነውና። ፳በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል። ፳፩አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና። ፳፪ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ። የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።