፩ፋሲካም የሚባለው የቂጣ በዓል ቀረበ። ፪የካህናት አለቆችና ጻፎችም እንዴት እንዲያጠፉት ይፈልጉ ነበር፤ ሕዝቡን ይፈሩ ነበርና። ፫ሰይጣንም ከአሥራ ሁለቱ ቍጥር አንዱ በነበረው የአስቆሮቱ በሚባለው በይሁዳ ገባ፤ ፬ሄዶም እንዴት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ከካህናት አለቆችና ከመቅደስ አዛዦች ጋር ተነጋገረ። ፭እነርሱም ደስ አላቸው፥ ገንዘብም ሊሰጡት ተዋዋሉ። ፮እሺም አለ፥ ሕዝብም በሌለበት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ምቹ ጊዜ ይፈልግ ነበር። ፯ፋሲካንም ሊያርዱበት የሚገባው የቂጣ በዓል ደረሰ፤ ፰ጴጥሮስንና ዮሐንስንም። ፋሲካን እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን ብሎ ላካቸው። ፱እነርሱም። ወዴት እናዘጋጅ ዘንድ ትወዳለህ? አሉት። ፲እርሱም አላቸው። እነሆ፥ ወደ ከተማ ስትገቡ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደ ሚገባበት ቤት ተከተሉት፤ ፲፩ለባለቤቱም። መምህሩ። ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል በሉት፤ ፲፪ያም በደርብ ላይ ያለውን የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን። ፲፫ሄደውም እንዳላቸው አገኙና ፋሲካን አሰናዱ። ፲፬ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በማዕድ ተቀመጠ። ፲፭እርሱም። ከመከራዬ በፊት ከእናንተ ጋር ይህን ፋሲካ ልበላ እጅግ እመኝ ነበር፤ ፲፮እላችኋለሁና፥ በእግዚአብሔር መንግሥት እስኪፈጸም ድረስ፥ ወደ ፊት ከዚህ አልበላም አላቸው። ፲፯ጽዋንም ተቀበለ አመስግኖም። ይህን እንካችሁ በመካከላችሁም ተካፈሉት፤ ፲፰እላችኋለሁና፥ የእግዚአብሔር መንግሥት እስክትመጣ ድረስ ከአሁን ጀምሮ ከወይኑ ፍሬ አልጠጣም አለ። ፲፱እንጀራንም አንሥቶ አመሰገነ ቆርሶም ሰጣቸውና። ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት አለ። ፳እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ። ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው። ፳፩ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ እጅ እነሆ በማዕድ ከእኔ ጋር ናት። ፳፪የሰው ልጅስ እንደ ተወሰነው ይሄዳል፥ ነገር ግን አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት። ፳፫ከእነርሱም ይህን ሊያደርግ ያለው ማን እንደ ሆነ እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር። ፳፬ደግሞም ማናቸውም ታላቅ ሆኖ እንዲቈጠር በመካከላቸው ክርክር ሆነ። ፳፭እንዲህም አላቸው። የአሕዛብ ነገሥታት ይገዙአቸዋል፥ በላያቸውም የሚሠለጥኑት ቸርነት አድራጊዎች ይባላሉ። ፳፮እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ፤ ነገር ግን ከእናንተ ታላቅ የሆነ በመካከላችሁ እንደ ታናሽ፥ የሚገዛም እንደሚያገለግል ይሁን። ፳፯በማዕድ የተቀመጠ ወይስ የሚያገለግል ማናቸው ታላቅ ነው? የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ። ፳፰ነገር ግን እናንተ በፈተናዎቼ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ፤ ፳፱-፴፩ጌታም። ስምዖን ስምዖን ሆይ፥ እነሆ፥ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ ፴፪እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አጽና አለ። ፴፫እርሱም። ጌታ ሆይ፥ ወደ ወኅኒም ወደ ሞትም ከአንተ ጋር ለመሄድ የተዘጋጀሁ ነኝ አለው። ፴፬እርሱ ግን። ጴጥሮስ ሆይ፥ እልሃለሁ፥ እንዳታውቀኝ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዛሬ ዶሮ አይጮኽም አለው። ፴፭ደግሞም። ያለ ኮረጆና ያለ ከረጢት ያለ ጫማም በላክኋችሁ ጊዜ፥ አንዳች ጐደለባችሁን? አላቸው። እነርሱም። አንዳች እንኳ አሉ። ፴፮እርሱም። አሁን ግን ኮረጆ ያለው ከእርሱ ጋር ይውሰድ፥ ከረጢትም ያለው እንዲሁ፤ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ሰይፍ ይግዛ። ፴፯እላችኋለሁና፥ ይህ። ከዓመፀኞች ጋር ተቈጠረ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ሊፈጸም ግድ ነው፤ አዎን፥ ስለ እኔ የሚሆነው አሁን ይፈጸማልና አላቸው። ፴፰እነርሱም። ጌታ ሆይ፥ እነሆ፥ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ አሉት። እርሱም። ይበቃል አላቸው። ፴፱ወጥቶም እንደ ልማዱ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ደግሞ ተከተሉት። ፵ወደ ስፍራውም ደርሶ። ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ አላቸው። ፵፩ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ የሚያህል ራቀ፥ ተንበርክኮም። አባት ሆይ፥ ፵፪ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር። ፵፫ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታ መልአክ ታየው። ፵፬በፍርሃትም ሲጣጣር አጽንቶ ይጸልይ ነበር፤ ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ። ፵፭ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣና ከኀዘን የተነሣ ተኝተው ሲያገኛቸው። ፵፮ስለ ምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ አላቸው። ፵፯ገናም ሲናገር እነሆ፥ ሰዎች መጡ፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱም ይሁዳ የሚባለው ይቀድማቸው ነበር፥ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ቀረበ። ፵፰ኢየሱስ ግን። ይሁዳ ሆይ፥ በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን? አለው። ፵፱በዙሪያውም የነበሩት የሚሆነውን ባዩ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ በሰይፍ እንምታቸውን? አሉት። ፶ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው። ፶፩ኢየሱስ ግን መልሶ። ይህንስ ፍቀዱ አለ፤ ጆሮውንም ዳስሶ ፈወሰው። ፶፪ኢየሱስም ወደ እርሱ ለመጡበት ለካህናት አለቆችና ለመቅደስ አዛዦች ለሽማግሌዎችም። ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ወጣችሁን? ፶፫በመቅደስ ዕለት ዕለት ከእናንተ ጋር ስሆን እጆቻችሁን አልዘረጋችሁብኝም፤ ይህ ግን ጊዜያችሁና የጨለማው ሥልጣን ነው አላቸው። ፶፬ይዘውም ወሰዱት ወደ ሊቀ ካህናት ቤትም አገቡት፤ ጴጥሮስም ርቆ ይከተለው ነበር። ፶፭በግቢ መካከልም እሳት አንድደው በአንድነት ተቀምጠው ሳሉ ጴጥሮስ በመካከላቸው ተቀመጠ። ፶፮በብርሃኑም በኩል ተቀምጦ ሳለ አንዲት ገረድ አየችውና ትኵር ብላ። ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ አለች። ፶፯እርሱ ግን። አንቺ ሴት፥ አላውቀውም ብሎ ካደ። ፶፰ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሌላው አይቶት። አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህ አለው። ጴጥሮስ ግን። አንተ ሰው፥ እኔ አይደለሁም አለ። ፶፱አንድ ሰዓትም የሚያህል ቆይቶ ሌላው አስረግጦ። እርሱ የገሊላ ሰው ነውና በእውነት ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ አለ። ፷ጴጥሮስ ግን። አንተ ሰው፥ የምትለውን አላውቅም አለ። ያን ጊዜም ገና ሲናገር ዶሮ ጮኸ። ፷፩ጌታም ዘወር ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም። ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እንዳለው የጌታ ቃል ትዝ አለው። ፷፪ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ። ፷፫ኢየሱስንም የያዙት ሰዎች ይዘብቱበትና ይደበድቡት ነበር፤ ፷፬ሸፍነውም ፊቱን ይመቱት ነበርና። በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገር እያሉ ይጠይቁት ነበር። ፷፭ሌላም ብዙ ነገር እየተሳደቡ በእርሱ ላይ ይናገሩ ነበር። ፷፮በነጋም ጊዜ የሕዝቡ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቆች ጻፎችም ተሰብስበው ወደ ሸንጎአቸው ወሰዱትና ፷፯ክርስቶስ አንተ ነህን? ንገረን አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው። ብነግራችሁ አታምኑም፤ ፷፰ብጠይቅም አትመልሱልኝም አትፈቱኝምም። ፷፱ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኃይል ቀኝ ይቀመጣል። ፸ሁላቸውም። እንግዲያስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን? አሉት። እርሱም። እኔ እንደ ሆንሁ እናንተ ትላላችሁ አላቸው። ፸፩እነርሱም። ራሳችን ከአፉ ሰምተናልና ከእንግዲህ ወዲህ ምን ምስክር ያስፈልገናል? አሉ።