፩በዚያ ወራት ደግሞ ብዙ ሕዝብ ነበረ የሚበሉትም ስለሌላቸው ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ። ፪ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ ፫ከእነርሱም አንዳንዶቹ ከሩቅ መጥተዋልና ጦማቸውን ወደ ቤታቸው ባሰናብታቸው በመንገድ ይዝላሉ አላቸው። ፬ደቀ መዛሙርቱም። በዚህ በምድረ በዳ እንጀራ ከየት አግኝቶ ሰው እነዚህን ማጥገብ ይችላል? ብለው መለሱለት። ፭እርሱም። ስንት እንጀራ አላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው፥ እነርሱም። ሰባት አሉት። ፮ሕዝቡም በምድር እንዲቀመጡ አዘዘ። ሰባቱንም እንጀራ ይዞ አመሰገነ፥ ቈርሶም እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ለሕዝቡም አቀረቡ። ፯ጥቂትም ትንሽ ዓሣ ነበራቸው፤ ባረከውም ይህንም ደግሞ እንዲያቀርቡላቸው አዘዘ። ፰በሉም ጠገቡም፥ የተረፈውንም ቍርስራሽ ሰባት ቅርጫት አነሡ። ፱የበሉትም አራት ሺህ ያህል ነበሩ። ፲አሰናበታቸውም። ወዲያውም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ዳልማኑታ አገር መጣ። ፲፩ፈሪሳውያንም ወጡና ሊፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ፈልገው ከእርሱ ጋር ይከራከሩ ጀመር። ፲፪በመንፈሱም እጅግ ቃተተና። ይህ ትውልድ ስለ ምን ምልክት ይፈልጋል? እውነት እላችኋለሁ፥ ለዚህ ትውልድ ምልክት አይሰጠውም አለ። ፲፫ትቶአቸውም እንደ ገና ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ማዶ ሄደ። ፲፬እንጀራ መያዝም ረሱ፥ ለእነርሱም ከአንድ እንጀራ በቀር በታንኳይቱ አልነበራቸውም። ፲፭እርሱም። ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ ብሎ አዘዛቸው። ፲፮እርስ በርሳቸውም። እንጀራ ስለሌለን ይሆናል ብለው ተነጋገሩ። ፲፯ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው። እንጀራ ስለሌላችሁ ስለ ምን ትነጋገራላችሁ? ገና አልተመለከታችሁምን? አላስተዋላችሁምን? ፲፰ልባችሁስ ደንዝዞአልን? ዓይን ሳላችሁ አታዩምን? ጆሮስ ሳላችሁ አትሰሙምን? ትዝስ አይላችሁምን? ፲፱አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት መሶብ አነሣችሁ? እነርሱም። አሥራ ሁለት አሉት። ፳ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት ቅርጫት አነሣችሁ? እነርሱም። ሰባት አሉት። ፳፩ገና አላስተዋላችሁምን? አላቸው። ፳፪ወደ ቤተ ሳይዳም መጡ። ዕውርም አመጡለት፥ እንዲዳስሰውም ለመኑት። ፳፫ዕውሩንም እጁን ይዞ ከመንደር ውጭ አወጣው፥ በዓይኑም ተፍቶበት እጁንም ጭኖበት። አንዳች ታያለህን ብሎ ጠየቀው። ፳፬አሻቅቦም። ሰዎች እንደ ዛፍ ሲመላለሱ አያለሁ አለ። ፳፭ከዚህም በኋላ ደግሞ እጁን በዓይኑ ላይ ጫነበት አጥርቶም አየና ዳነም ከሩቅም ሳይቀር ሁሉን ተመለከተ። ፳፮ወደ ቤቱም ሰደደውና። ወደ መንደሩ አትግባ በመንደሩም ለማንም አንዳች አትናገር አለው። ፳፯ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም በፊልጶስ ቂሣርያ ወዳሉ መንደሮች ወጡ በመንገድም። ሰዎች እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው። ፳፰እነርሱም። መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ከነቢያት አንዱ ብለው ነገሩት። ፳፱እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም። አንተ ክርስቶስ ነህ ብሎ መለሰለት። ፴ስለ እርሱም ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። ፴፩የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ ከሽማግሌዎችም ከካህናት አለቆችም ከጻፎችም ሊጣል፥ ሊገደልም ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሣ እንዲገባው ያስተምራቸው ጀመር፤ ቃሉንም ገልጦ ይናገር ነበር። ፴፪ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ ይገሥጸው ጀመር። ፴፫እርሱ ግን ዘወር አለ ደቀ መዛሙርቱንም አይቶ ጴጥሮስን ገሠጸውና። ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና አለው። ፴፬ሕዝቡንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ እንዲህ አላቸው። በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። ፴፭ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን ያድናታል። ፴፮ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ፴፯ሰውስ ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? ፴፰በዚህም በዘማዊና በኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በአባቱ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር በመጣ ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል።