ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ፥ አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ። በነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፥ ከተጨረሱም በኋላ ተራበ። ዲያብሎስም። የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ ይህን ድንጋይ። እንጀራ ሁን ብለህ እዘዝ አለው። ኢየሱስም። ሰው በእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል ብሎ መለሰለት። ዲያብሎስም ረጅም ወደ ሆነ ተራራ አውጥቶ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው። ዲያብሎስም። ይህ ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውም ለእኔ ተሰጥቶአል ለምወደውም ለማንም እሰጠዋለሁና ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ስለዚህ አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ፥ ሁሉ ለአንተ ይሆናል አለው። ኢየሱስም መልሶ። ለጌታ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአል አለው። ፱-፲፪ኢየሱስም መልሶ። ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎአል አለው። ፲፫ዲያቢሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ። ፲፬ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለችው አገር ሁሉ ዝና ወጣ። ፲፭እርሱም በምኵራባቸው ያስተምር፥ ሁሉም ያመሰግኑት ነበር። ፲፮ወዳደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ፥ ሊያነብም ተነሣ። ፲፯-፳መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር። ፳፩እርሱም። ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ ይላቸው ጀመር። ፳፪ሁሉም ይመሰክሩለት ነበር ከአፉም ከሚወጣው ከጸጋው ቃል የተነሣ እየተደነቁ። ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን? ይሉ ነበር። ፳፫እርሱም። ያለ ጥርጥር ይህን ምሳሌ። ባለ መድኃኒት ሆይ፥ ራስህን ፈውስ፤ በቅፍርናሆም እንዳደረግኸው የሰማነውን ሁሉ በዚህ በገዛ አገርህ ደግሞ አድርግ ትሉኛላችሁ አላቸው። ፳፬እንዲህም አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ ነቢይ በገዛ አገሩ ከቶ አይወደድም። ፳፭ነገር ግን እውነት እላችኋለሁ፥ በኤልያስ ዘመን ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሰማይ ተዘግቶ ሳለ በምድር ሁሉ ብርቱ ራብ በነበረ ጊዜ፥ በእስራኤል ብዙ መበለቶች ነበሩ፤ ፳፮ኤልያስም በሲዶና አገር ወዳለች ወደ ሰራፕታ ወደ አንዲት መበለት እንጂ ከእነርሱ ወደ አንዲቱ አልተላከም። ፳፯በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመንም በእስራኤል ብዙ ለምጻሞች ነበሩ፥ ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ከእነርሱ አንድ ስንኳ አልነጻም። ፳፰በምኵራብም የነበሩ ሁሉ ይህን ሰምተው ቍጣ ሞላባቸው፥ ተነሥተውም ከከተማ ወደ ውጭ አወጡት፥ ፳፱ይጥሉትም ዘንድ ከተማቸው ተሠርታባት ወደ ነበረች ወደ ተራራው አፋፍ ወሰዱት፤ እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ። ፴፩ወደ ገሊላ ከተማም ወደ ቅፍርናሆም ወረደ። በሰንበትም ያስተምራቸው ነበር፤ ፴፪ቃሉ በሥልጣን ነበርና በትምህርቱ ተገረሙ። ፴፫በምኵራብም የርኵስ ጋኔን መንፈስ ያደረበት ሰው ነበረ፥ በታላቅ ድምፅም ጮኾ። ፴፬ተው፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄሃለሁ፥ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱሱ አለ። ፴፭ኢየሱስም። ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም በመካከላቸው ጥሎት ሳይጐዳው ከእርሱ ወጣ። ፴፮ሁሉንም መደነቅ ያዛቸው፥ እርስ በርሳቸውም። ይህ ቃል ምንድር ነው? በሥልጣንና በኃይል ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛልና፥ ይወጡማል ብለው ተነጋገሩ። ፴፯ዝናም በዙሪያው ባለች አገር ወደ ስፍራው ሁሉ ስለ እርሱ ወጣ። ፴፰በምኵራብም ተነሥቶ ወደ ስምዖን ቤት ገባ። የስምዖንም አማት በብርቱ ንዳድ ታማ ነበር ስለ እርስዋም ለመኑት። ፴፱በአጠገብዋም ቆሞ ንዳዱን ገሠጸውና ለቀቃት፤ ያንጊዜውንም ተነሥታ አገለገለቻቸው። ፀሐይም በገባ ጊዜ በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙ በሽተኞችን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡአቸው፤ እርሱም በእያንዳቸው ላይ እጁን ጭኖ ፈወሳቸው። ፵፩አጋንንትም ደግሞ። አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ እየጮኹም ከብዙዎች ይወጡ ነበር፤ ገሠጻቸውም ክርስቶስም እንደ ሆነ አውቀውት ነበርና እንዲናገሩ አልፈቀደላቸውም። ፵፪በጸባም ጊዜ ወጥቶ ወደ ምድረ በዳ ሄደ፤ ሕዝቡም ይፈልጉት ነበር፤ ወደ እርሱም መጡ፥ ከእነርሱም ተለይቶ እንዳይሄድ ሊከለክሉት ወደዱ። ፵፫እርሱ ግን። ስለዚህ ተልኬአለሁና ለሌሎቹ ከተማዎች ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እሰብክ ዘንድ ይገባኛል አላቸው። ፵፬በገሊላም ምኵራቦች ይሰብክ ነበር።