፩ሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃል እየሰሙ ሲያስጠብቡት ሳሉ፥ እርሱ ራሱ በጌንሳሬጥ ባሕር ዳር ቆሞ ነበር፤ ፪በባሕር ዳርም ቆመው የነበሩትን ሁለት ታንኳዎች አየ፤ ዓሣ አጥማጆች ግን ከእነርሱ ውስጥ ወጥተው መረቦቻቸውን ያጥቡ ነበር። ፫ከታንኳዎቹም የስምዖን ወደ ነበረች ወደ አንዲቱ ገብቶ ከምድር ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ለመነው፤ በታንኳይቱም ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተምር ነበር። ፬ነገሩንም ከጨረሰ በኋላ፥ ስምዖንን። ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ አለው። ፭ስምዖንም መልሶ። አቤቱ፥ ሌሊቱን ሁሉ አድረን ስንደክም ምንም አልያዝንም፤ ነገር ግን በቃልህ መረቦቹን እጥላለሁ አለው። ፮ይህንም ባደረጉ ጊዜ እጅግ ብዙ ዓሣ ያዙ፤ መረቦቻቸውም ተቀደዱ። ፯በሌላ ታንኳም የነበሩትን ጓደኞቻቸውን መጥተው እንዲያግዙአቸው ጠቀሱ፤ መጥተውም ሁለቱ ታንኳዎች እስኪሰጥሙ ድረስ ሞሉአቸው። ፰ስምዖን ጴጥሮስ ግን ባየ ጊዜ በኢየሱስ ጕልበት ላይ ወድቆ። ጌታ ሆይ፥ እኔ ኃጢአተኛ ነኝና ከኔ ተለይ አለው። ፱ስላጠመዱት ዓሣ እርሱ ከእርሱ ጋርም የነበሩ ሁሉ ተደንቀዋልና፥ ፲እንዲሁም ደግሞ የስምዖን ባልንጀሮች የነበሩ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ተደነቁ። ኢየሱስም ስምዖንን። አትፍራ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ አለው። ፲፩ታንኳዎችንም ወደ ምድር አድርሰው ሁሉን ትተው ተከተሉት። ፲፪ከከተማዎችም በአንዲቱ ሳለ፥ እነሆ፥ ለምጽ የሞላበት ሰው ነበረ፤ ኢየሱስንም አይቶ በፊቱ ወደቀና። ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ፥ ልታነጻኝ ትችላለህ ብሎ ለመነው። ፲፫እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና። እወዳለሁ፥ ንጻ አለው፤ ወዲያውም ለምጹ ለቀቀው። ፲፬እርሱም ለማንም እንዳይናገር አዘዘው፥ ነገር ግን። ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ እንዳዘዘ መሥዋዕት አቅርብ አለው። ፲፭ወሬው ግን አብዝቶ ወጣ፥ ብዙ ሕዝብም ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ ይሰበሰቡ ነበር፤ ፲፮ነገር ግን እርሱ ወደ ምድረ በዳ ፈቀቅ ብሎ ይጸልይ ነበር። ፲፯አንድ ቀንም ያስተምር ነበር፤ ከገሊላና ከይሁዳ መንደሮችም ሁሉ ከኢየሩሳሌምም መጥተው የነበሩ ፈሪሳውያንና የሕግ መምህራን ይቀመጡ ነበር፤ እርሱም እንዲፈውስ የጌታ ኃይል ሆነለት። ፲፰እነሆም፥ አንድ ሽባ በአልጋ ተሸክመው አመጡ፤ አግብተውም በፊቱ ሊያኖሩት ይሹ ነበር። ፲፱ስለ ሕዝቡም ብዛት እንዴት አድርገው እንዲያገቡት ሲያቅታቸው፥ ወደ ሰገነቱ ወጡ የጣራውንም ጡብ አሳልፈው በመካከል በኢየሱስ ፊት ከነአልጋው አወረዱት። ፳እምነታቸውንም አይቶ። አንተ ሰው፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው። ፳፩ጻፎችና ፈሪሳውያንም። ይህ የሚሳደብ ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል? ብለው ያስቡ ጀመር። ፳፪ኢየሱስም አሳባቸውን እያወቀ መልሶ። በልባችሁ ምን ታስባላችሁ? ፳፫ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ከማለት ወይስ። ተነሣና ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል? ፳፬ነገር ግን በምድር ላይ ኃጢአት ሊያስተሰርይ ለሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ብሎ፥ ሽባውን። አንተን እልሃለሁ፥ ነተሣ፥ አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ አለው። ፳፭በዚያን ጊዜም በፊታቸው ተነሣ፥ ተኝቶበትም የነበረውን ተሸክሞ እግዚአብሔርን እያመሰገነ ወደ ቤቱ ሄደ። ፳፮ሁሉንም መገረም ያዛቸው፥ እግዚአብሔርንም አመስግነው። ዛሬስ ድንቅ ነገር አየን እያሉ ፍርሃት ሞላባቸው። ፳፯ከዚህም በኋላ ወጥቶ ሌዊ የሚባል ቀራጭ በመቅረጫው ተቀምጦ ተመለከተና። ተከተለኝ አለው። ፳፰ሁሉንም ተወ፤ ተነሥቶም ተከተለው። ፳፱ሌዊም በቤቱ ታላቅ ግብዣ አደረገለት፤ ከእነርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩ ከቀራጮችና ከሌሎች ሰዎች ብዙ ሕዝብ ነበሩ። ፴ፈሪሳውያንና ጻፎቻቸውም በደቀ መዛሙርቱ ላይ። ስለ ምን ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ትበላላችሁ ትጠጡማላችሁ? ብለው አንጐራጐሩ። ፴፩ኢየሱስም መልሶ። ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤ ፴፪ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው። ፴፫እነርሱም። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ስለ ምን ብዙ ይጦማሉ ጸሎትስ ስለ ምን ያደርጋሉ፥ ደግሞም የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ስለ ምን እንደዚሁ ያደርጋሉ፤ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን ይበላሉ ይጠጣሉም? አሉት። ፴፬ኢየሱስም። ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎችን ልታስጦሙ ትችላላችሁን? ፴፭ነገር ግን ወራት ይመጣል፥ ሙሽራውም ከእነርሱ ሲወሰድ ያንጊዜ፥ በዚያ ወራት ይጦማሉ አላቸው። ፴፮ደግሞም ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው። የአዲስ ልብስ እራፊ ባረጀ ልብስ ላይ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አዲሱን ይቀደዋል ደግሞም አዲስ እራፊ ለአሮጌው አይስማማውም። ፴፯ባረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አዲሱ የወይን ጠጅ አቁማዳውን ያፈነዳል፥ እርሱም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል። ፴፰አዲሱን የወይን ጠጅ ግን በአዲስ አቁማዳ ማኖር ይገባል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ። ፴፱አሮጌ የወይን ጠጅ ሲጠጣ አዲሱን የሚሻ ማንም የለም፤ አሮጌው ይጣፍጣል ይላልና።