በሰንበትም በእርሻ መካከል ያልፍ ነበር ደቀ መዛሙርቱም እሸት ይቀጥፉ በእጃቸውም እያሹ ይበሉ ነበር። ከፈሪሳውያን ግን አንዳንዶቹ። በሰንበት ሊያደርግ ያልተፈቀደውን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? አሉአቸው። ፫-፭የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው አላቸውም። በሌላው ሰንበትም ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ፤ በዚያም ቀኝ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ጻፎችና ፈሪሳውያንም መክሰሻ ሊያገኙበት በሰንበት ይፈውስ እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር። እርሱ ግን አሳባቸውን አውቆ እጁ የሰለለችውን ሰው። ተነሣና በመካከል ቁም አለው፤ ተነሥቶም ቆመ። ኢየሱስም። እጠይቃችኋለሁ፤ በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን ወይስ ክፉ? ነፍስ ማዳንን ወይስ መግደል? አላቸው። ሁላቸውንም ዙሪያውን አየና ሰውዬውን። እጅህን ዘርጋ አለው። እርሱም እንዲህ አደረገ፥ እጁም እንደ ሁለተኛይቱ ዳነች። ፲፩እነርሱም ቍጣ ሞላባቸው፥ በኢየሱስም ምን እንዲያደርጉበት እርስ በርሳቸው ተባባሉ። ፲፪በነዚህም ወራት ይጸልይ ዘንድ ወደ ተራራ ወጣ፥ ሌሊቱንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሲጸልይ አደረ። ፲፫በነጋም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ጠራ፥ ከእነርሱም አሥራ ሁለት መረጠ ደግሞም ሐዋርያት ብሎ ሰየማቸው፤ ፲፬እነርሱም፥ ጴጥሮስ ብሎ እንደ ገና የሰየመው ስምዖን፥ ወንድሙም እንድርያስ፥ ያዕቆብም ዮሐንስም፥ ፊልጶስም በርተሎሜዎስም፥ ፲፭ማቴዎስም ቶማስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም ቀናተኛ የሚባለው ስምዖንም፥ ፲፮የያዕቆብ ይሁዳም፥ አሳልፎ የሰጠውም የአስቆሮቱ ይሁዳ ናቸው። ፲፯ከእነርሱም ጋር ወርዶ በተካከለ ስፍራ ቆመ፥ ከደቀ መዛሙርቱም ወገን ብዙ ሕዝብ ነበረ፥ ደግሞም ሊሰሙትና ከደዌአቸው ሊፈወሱ ከይሁዳ ሁሉ ከኢየሩሳሌምም ከጢሮስና ከሲዶና ባሕር ዳርም የመጡ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ፲፰ከርኵሳንም መናፍስት ይሠቃዩ የነበሩት ተፈወሱ፤ ፲፱ከእርሱም ኃይል ወጥቶ ሁሉን ይፈውስ ነበርና ሕዝቡ ሁሉ ሊዳስሱት ይሹ ነበር። እርሱም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዓይኑን አነሣ እንዲህም አላቸው። እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና። ፳፩እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፥ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፥ ትስቃላችሁና። ፳፪ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ ሲለዩአችሁም ሲነቅፉአችሁም ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ፥ ብፁዓን ናችሁ። ፳፫እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ዝለሉም፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና። ፳፬ነገር ግን እናንተ ባለ ጠጎች ወዮላችሁ፥ መጽናናታችሁን ተቀብላችኋልና። ፳፭እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ፥ ትራባላችሁና። እናንተ አሁን የምትስቁ ወዮላችሁ፥ ታዝናላችሁና ታለቅሱማላችሁ። ፳፮ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ፥ ወዮላችሁ፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና። ፳፯ነገር ግን ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፥ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ለሚጠሉአችሁ መልካም አድርጉ፥ ፳፰የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ስለሚበድሉአችሁም ጸልዩ። ፳፱ጕንጭህን ለሚመታህ ደግሞ ሁለተኛውን ስጠው፥ መጐናጸፊያህንም ለሚወስድ እጀ ጠባብህን ደግሞ አትከልክለው። ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ፥ ገንዘብህንም የሚወስድ እንዲመልስ አትጠይቀው። ፴፩ሰዎችም ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው። ፴፪የሚወዱአችሁንማ ብትወዱ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ የሚወዱአቸውን ይወዳሉና። ፴፫መልካምም ለሚያደርጉላችሁ መልካም ብታደርጉ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ ያን ያደርጋሉና። ፴፬እንድትወስዱባቸው ተስፋ ለምታደርጉአቸው ብታበድሩ፥ ምን ምስጋና አላችሁ? ኃጢአተኞች ደግሞ በትክክል እንዲቀበሉ ለኃጢአተኞች ያበድራሉ። ፴፭ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ፤ ምንም ተስፋ ሳታደርጉም አበድሩ፥ ዋጋችሁም ታላቅ ይሆናል፥ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፥ እርሱ ለማያመሰግኑ ለክፉዎችም ቸር ነውና። ፴፮አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ ርኅሩኆች ሁኑ። ፴፯አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም፤ አትኰንኑ አትኰነኑምም። ይቅር በሉ ይቅርም ትባላላችሁ። ፴፰ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና፥ የተጨቈነና የተነቀነቀ የተትረፈረፈም መልካም መስፈሪያ በእቅፋችሁ ይሰጣችኋል። ፴፱ምሳሌም አላቸው። ዕውር ዕውርን ሊመራ ይችላልን? ሁለቱ በጕድጓድ አይወድቁምን? ደቀ መዝሙር ከመምህሩ አይበልጥም፤ ፈጽሞ የተማረ ሁሉ ግን እንደ መምህሩ ይሆናል። ፵፩በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለ ምን ታያለህ፥ በራስህ ዓይን ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም? ፵፪በዓይንህ ያለውን ምሰሶ ራስህ ሳታይ፥ እንዴት ወንድምህን። ወንድሜ ሆይ፥ በዓይንህ ያለውን ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ ልትል ትችላለህ? አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ ከዚያም በኋላ በወንድምህ ዓይን ያለውን ጉድፍ ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ። ፵፫ክፉ ፍሬ የሚያደርግ መልካም ዛፍ የለምና፥ እንዲሁም መልካም ፍሬ የሚያደርግ ክፉ ዛፍ የለም። ፵፬ዛፍ ሁሉ ከፍሬው ይታወቃልና፤ ከእሾህ በለስ አይለቅሙም፥ ከአጣጥ ቍጥቋጦም ወይን አይቈርጡም። ፵፭በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፉ ይናገራልና መልካም ሰው ከልብ መልካም መዝገብ መልካሙን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከልብ ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል። ፵፮ስለ ምን። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ ትሉኛላችሁ፥ የምለውንም አታደርጉም? ፵፯ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ ቃሌንም ሰምቶ የሚያደርገው፥ ማንን እንዲመስል አሳያችኋለሁ። ፵፰ቤት ሲሠራ አጥልቆ የቆፈረ በዓለት ላይም የመሠረተ ሰውን ይመስላል፤ ጐርፍም በመጣ ጊዜ ወንዙ ያን ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ ሊያናውጠው አልቻለም። ፵፱ሰምቶ የማያደርገው ግን ያለ መሠረት በምድር ላይ ቤቱን የሠራ ሰውን ይመስላል፤ ወንዙም ገፋው ወዲያውም ወደቀ የዚያ ቤት አወዳደቅም ታላቅ ሆነ።