ቃሉን ሁሉ በሕዝብ ጆሮዎች በጨረሰ ጊዜ ወደ ቅፍርናሆም ገባ። አንድ የመቶ አለቃም ነበረ፤ የሚወደውም ባሪያው ታሞ ሊሞት ቀርቦ ነበር። ስለ ኢየሱስም በሰማ ጊዜ የአይሁድን ሽማግሎች ወደ እርሱ ላከና መጥቶ ባሪያውን እንዲያድን ለመነው። እነርሱም ወደ ኢየሱስ መጥተው። ይህን ልታደርግለት ይገባዋል፤ ሕዝባችንን ይወዳልና ምኵራብም ራሱ ሠርቶልናል ብለው አጽንተው ለመኑት። ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ሄደ። አሁንም ወደ ቤቱ በቀረበ ጊዜ የመቶው አለቃ ወዳጆቹን ወደ እርሱ ላከ፤ አለውም። ጌታ ሆይ በቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና አትድከም፤ ስለዚህም ወደ አንተ ልመጣ እንዲገባኝ ሰውነቴን አልቈጠርሁትም፤ ነገር ግን ቃል ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ደግሞ ከሌሎች በታች የምገዛ ሰው ነኝ፥ ከእኔም በታች ወታደሮች አሉኝ፥ አንዱንም። ሂድ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም። ና ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬንም። ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል። ኢየሱስም ይህን ሰምቶ በእርሱ ተደነቀ፥ ዘወርም ብሎ ለተከተሉት ሕዝብ። እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም አላቸው። የተላኩትም ወደ ቤት ተመልሰው ባሪያውን ባለ ጤና ሆኖ አገኙት። ፲፩በነገውም ናይን ወደምትባል ወደ አንዲት ከተማ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም ብዙ ሕዝብም ከእርሱ ጋር አብረው ሄዱ። ፲፪ወደ ከተማይቱም በር በቀረበ ጊዜ፥ እነሆ፥ የሞተ ሰው ተሸክመው አወጡ፤ እርሱም ለእናቱ አንድ ልጅ ነበረ፥ እርስዋም መበለት ነበረች፥ ብዙም የከተማ ሕዝብ ከእርስዋ ጋር አብረው ነበሩ። ፲፫ጌታም ባያት ጊዜ አዘነላትና። አታልቅሽ አላት። ፲፬ቀርቦም ቃሬዛውን ነካ፥ የተሸከሙትም ቆሙ፤ አለውም። አንተ ጐበዝ፥ እልሃለሁ፥ ተነሣ። ፲፭የሞተውም ቀና ብሎ ተቀመጠ ሊናገርም ጀመረ፥ ለእናቱም ሰጣት። ፲፮ሁሉንም ፍርሃት ያዛቸውና። ታላቅ ነቢይ በእኛ መካከል ተነሥቶአል፥ ደግሞ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ጐበኘ እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ፲፯ይህም ዝና ስለ እርሱ በይሁዳ ሁሉ በዙሪያውም ባለች አገር ሁሉ ወጣ። ፲፰ደቀ መዛሙርቱም ለዮሐንስ እነዚህን ሁሉ አወሩ። ፲፱ዮሐንስም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ወደ እርሱ ጠርቶ። የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላውን እንጠብቅ? ብሎ ወደ ኢየሱስ ላከ። ሰዎቹም ወደ እርሱ መጥተው። መጥምቁ ዮሐንስ። የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላውን እንጠብቅ? ብሎ ወደ አንተ ላከን አሉት። ፳፩በዚያች ሰዓት ከደዌና ከሥቃይ ከክፉዎች መናፍስትም ብዙዎችን ፈወሰ፥ ለብዙ ዕውሮችም ማየትን ሰጠ። ፳፪ኢየሱስም መልሶ። ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ ዕውሮች ያያሉ፥ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ፥ ደንቆሮዎችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ፥ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ ፳፫በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው አላቸው። ፳፬የዮሐንስ መልክተኞችም ከሄዱ በኋላ፥ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ይናገር ጀመር እንዲህም አለ። ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ፳፭ቀጭን ልብስ የለበሰውን ሰውን? እነሆ፥ ጌጠኛ ልብስ የሚለብሱና በቅምጥልነት የሚኖሩ በነገሥታት ቤት አሉ። ፳፮ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፥ ከነቢይም የሚበልጠውን። ፳፯እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነው። ፳፰እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። ፳፱የሰሙትም ሕዝብ ሁሉ ቀራጮች እንኳ ሳይቀሩ በዮሐንስ ጥምቀት ተጠምቀው እግዚአብሔርን አጸደቁ፤ ፈሪሳውያንና ሕግ አዋቂዎች ግን በእርሱ ስለ አልተጠመቁ የእግዚአብሔርን ምክር ከራሳቸው ጣሉ። ፴፩እንግዲህ የዚችን ትውልድ ሰዎች በምን አስመስላቸዋለሁ? ማንንስ ይመስላሉ? ፴፪በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፥ እርስ በርሳቸውም እየተጠራሩ። እንቢልታ ነፋንላችሁ አልዘፈናችሁምም፤ ሙሾ አወጣንላችሁ አላለቀሳችሁምም ይላል። ፴፫መጥምቁ ዮሐንስ እንጀራ ሳይበላ የወይን ጠጅም ሳይጠጣ መጥቶ ነበርና። ጋኔን አለበት አላችሁት። ፴፬የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጥቶአልና። እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ አላችሁት። ፴፭ጥበብም ለልጆችዋ ሁሉ ጸደቀች። ፴፮ከፈሪሳውያንም አንድ ከእርሱ ጋር ይበላ ዘንድ ለመነው፤ በፈሪሳዊው ቤትም ገብቶ በማዕድ ተቀመጠ። ፴፯እነሆም በዚያች ከተማ ኃጢአተኛ የነበረች አንዲት ሴት፤ በፈሪሳዊው ቤት በማዕድ እንደ ተቀመጠ ባወቀች ጊዜ፥ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ አመጣች። ፴፰በስተ ኋላውም በእግሩ አጠገብ ቆማ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመረች፥ በራስ ጠጕርዋም ታብሰው እግሩንም ትስመው ሽቱም ትቀባው ነበረች። ፴፱የጠራው ፈሪሳዊም አይቶ። ይህስ ነቢይ ቢሆን፥ ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን እንደ ሆነች እንዴትስ እንደ ነበረች ባወቀ ነበር፥ ኃጢአተኛ ናትና ብሎ በልቡ አሰበ። ኢየሱስም መልሶ። ስምዖን ሆይ፥ የምነግርህ ነገር አለኝ አለው። እርሱም። መምህር ሆይ፥ ተናገር አለ። ፵፩ለአንድ አበዳሪ ሁለት ተበዳሪዎች ነበሩት በአንዱ አምስት መቶ ዲናር ነበረበት በሁለተኛውም አምሳ። ፵፪የሚከፍሉትም ቢያጡ ለሁለቱም ተወላቸው። እንግዲህ ከእነርሱ አብልጦ የሚወደው ማንኛው ነው? ፵፫ስምዖንም መልሶ። ብዙ የተወለቱ ይመስለኛል አለ። እርሱም። በእውነት ፈረድህ አለው። ፵፬ወደ ሴቲቱም ዘወር ብሎ ስምዖንን እንዲህ አለው። ይህችን ሴት ታያለህን? እኔ ወደ ቤትህ ገባሁ፥ ውኃ ስንኳ ለእግሬ አላቀረብህልኝም፤ እርስዋ ግን በእንባዋ እግሬን አራሰች በጠጕርዋም አበሰች። ፵፭አንተ አልሳምኸኝም፤ እርስዋ ግን ከገባሁ ጀምራ እግሬን ከመሳም አላቋረጠችም። ፵፮አንተ ራሴን ዘይት አልቀባኸኝም፤ እርስዋ ግን እግሬን ሽቱ ቀባች። ፵፯ስለዚህ እልሃለሁ፥ እጅግ ወዳለችና ብዙ ያለው ኃጢአትዋ ተሰርዮላታል፤ ጥቂት ግን የሚሰረይለት ጥቂት ይወዳል። ፵፰እርስዋንም። ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል አላት። ፵፱ከእርሱም ጋር በማዕድ ተቀምጠው የነበሩት በልባቸው። ኃጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ ይህ ማን ነው? ይሉ ጀመር። ሴቲቱንም። እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ አላት።