አሥራ ሁለቱንም ሐዋርያት በአንድነት ወደ እርሱ ጠርቶ በአጋንንት ሁሉ ላይ ደዌንም ይፈውሱ ዘንድ ኃይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤ የእግዚአብሔርንም መንግሥት እንዲሰብኩና ድውዮችን እንዲፈውሱ ላካቸው፥ እንዲህም አላቸው። በትርም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ እንጀራም ቢሆን፥ ብርም ቢሆን ለመንገድ ምንም አትያዙ፥ ሁለት እጀ ጠባብም አይሁንላችሁ። በማናቸውም በምትገቡበት ቤት በዚያ ተቀመጡ ከዚያም ውጡ። ማናቸውም የማይቀበሉአችሁ ቢሆኑ፥ ከዚያ ከተማ ወጥታችሁ ምስክር እንዲሆንባቸው ከእግራችሁ ትቢያ አራግፉ። ወጥተውም ወንጌልን እየሰበኩና በስፍራው ሁሉ እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር። የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም የተደረገውን ነገር ሁሉ ሰምቶ፥ አንዳንድ ሰዎች። ዮሐንስ ከሙታን ተነሣ፥ ሌሎችም። ኤልያስ ተገለጠ፥ ሌሎችም። ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል ይሉ ስለ ነበሩ አመነታ። ሄሮድስም። ዮሐንስንስ እኔ ራሱን አስቈረጥሁት፤ ይህ እንዲህ ያለ ነገር የምሰማበት ማን ነው? አለ። ሊያየውም ይሻ ነበር። ሐዋርያትም ተመልሰው ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት። ከእርሱ ጋርም ወስዶአቸው ቤተ ሳይዳ ከምትባል ከተማ አጠገብ ወደ ምድረ በዳ ለብቻው ፈቀቅ አለ። ፲፩ሕዝቡም አውቀው ተከተሉት፤ ተቀብሎአቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፥ መፈወስ ያስፈለጋቸውንም ፈወሳቸው። ፲፪ቀኑም ይመሽ ጀመር፤ አሥራ ሁለቱም ቀርበው። በዚህ በምድረ በዳ ነንና በዙሪያችን ወዳሉ መንደሮችና ገጠሮች ሄደው እንዲያድሩና ምግብ እንዲያገኙ ሕዝቡን አሰናብት አሉት። ፲፫እርሱ ግን። እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው አላቸው። እነርሱም። ሄደን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ ምግብ ካልገዛን፥ ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ የሚበልጥ የለንም አሉት፤ ፲፬አምስት ሺህ ሰዎች ያህሉ ነበርና። ለደቀ መዛሙርቱ። በየክፍሉ አምሳ አምሳውን አስቀምጡአቸው አላቸው። ፲፭እንዲህም አደረጉ ሁሉንም አስቀመጡአቸው። ፲፮አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ፥ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረካቸው ቆርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛርሙርቱ ሰጠ። ፲፯ሁሉም በልተው ጠገቡ፥ ከእነርሱም የተረፈውን ቍርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ወሰዱ። ፲፰ለብቻውም ሲጸልይ ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩና። ሕዝቡ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ጠየቃቸው። ፲፱እነርሱም መልሰው። መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም። ኤልያስ፥ ሌሎችም። ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል ይላሉ አሉት። እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ። ከእግዚአብሔር የተቀባህ ነህ አለ። ፳፩-፳፫ለሁሉም እንዲህ አላቸው። በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ዕለት ዕለት ተሸክሞ ይከተለኝ። ፳፬ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፤ ስለ እኔ ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን እርሱ ያድናታል። ፳፭ሰው ዓለሙን ሁሉ አትርፎ ራሱን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ፳፮በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ በክብሩ በአባቱና በቅዱሳን መላእክቱ ክብርም ሲመጣ በእርሱ ያፍርበታል። ፳፯እውነት እላችኋለሁ፥ በዚህ ከሚቆሙት ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት እስኪያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ። ፳፰ከዚህም ቃል በኋላ ስምንት ቀን ያህል ቈይቶ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ያዕቆብንም ይዞ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። ፳፱ሲጸልይም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሁለት ሰዎች እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ ፴፩በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር። ፴፪ነገር ግን ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ከበደባቸው፤ ነቅተው ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ። ፴፫ከእርሱም ሲለዩ ጴጥሮስ ኢየሱስን። አቤቱ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው፤ የሚለውንም አያውቅም ነበር። ፴፬ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ሳሉ ፈሩ። ፴፭ከደመናውም። የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ። ፴፮ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ። እነርሱም ዝም አሉ ካዩትም ነገር በዚያ ወራት ምንም ለማንም አላወሩም። ፴፯በነገውም ከተራራ ሲወርዱ ብዙ ሕዝብ ተገናኙት። ፴፰እነሆም፥ ከሕዝቡ አንድ ሰው እንዲህ እያለ ጮኸ። መምህር ሆይ፥ ለእኔ አንድ ልጅ ነውና ልጄን እንድታይልኝ እለምንሃለሁ። ፴፱እነሆም፥ ጋኔን ይይዘዋል፥ ድንገትም ይጮኻል አረፋም እያስደፈቀው ያንፈራግጠዋል፥ እየቀጠቀጠም በጭንቅ ይለቀዋል፤ ደቀ መዛሙርትህንም እንዲያወጡት ለመንሁ፥ አልቻሉምም። ፵፩ኢየሱስም መልሶ። እናንተ የማታምን ጠማማ ትውልድ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጅህን ወደዚህ አምጣው አለ። ፵፪ሲቀርብም ጋኔኑ ጣለውና አንፈራገጠው፤ ኢየሱስ ግን ርኵሱን መንፈስ ገሥጾ ብላቴናውን ፈወሰው ለአባቱም መለሰው። ፵፫ሁሉም ከእግዚአብሔር ታላቅነት የተነሣ ተገረሙ። ሁሉም ኢየሱስ ባደረገው ሁሉ ሲደነቁ፥ ፵፬ለደቀ መዛሙርቱ። የሰው ልጅ በሰው እጅ ይሰጥ ዘንድ አለውና እናንተ ይህን ቃል በጆሮአችሁ አኑሩ አለ። ፵፭እነርሱ ግን ይህን ነገር አላስተዋሉም፥ እንዳይገባቸውም ተሰውሮባቸው ነበር፤ ስለዚህ ነገርም እንዳይጠይቁት ፈሩ። ፵፮ከእነርሱም ማን እንዲበልጥ ክርክር ተነሣባቸው። ፵፯ኢየሱስም የልባቸውን አሳብ አውቆ ሕፃንን ያዘ፤ በአጠገቡም አቁሞ። ፵፰ማንም ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን ይቀበላል፤ ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ታላቅ ነውና አላቸው። ፵፱ዮሐንስም መልሶ። አቤቱ፥ አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያወጣ አየነው፥ ከእኛ ጋርም ስለማይከተል ከለከልነው አለው። ኢየሱስ ግን። የማይቃወማችሁ ከእናንተ ጋር ነውና አትከልክሉት አለው። ፶፩የሚወጣበትም ወራት በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና፥ ፶፪በፊቱም መልክተኞችን ሰደደ። ሄደውም ሊያሰናዱለት ወደ አንድ ወደ ሳምራውያን መንደር ገቡ፤ ፶፫ፊቱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ስለ ነበረ አልተቀበሉትም። ፶፬ደቀ መዛሙርቱም ያዕቆብና ዮሐንስ አይተው። ጌታ ሆይ፥ ኤልያስ ደግሞ እንዳደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንል ዘንድ ትወዳለህን? አሉት። ፶፭እርሱ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸውና። ምን ዓይነት መንፈስ እንደ ሆነላችሁ አታውቁም፤ ፶፮የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም አለ። ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ። ፶፯እነርሱም በመንገድ ሲሄዱ አንድ ሰው። ጌታ ሆይ፥ ወደ ምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ አለው። ፶፰ኢየሱስም። ለቀበሮዎች ጕድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው። ፶፱ሌላውንም። ተከተለኝ አለው። እርሱ ግን። ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ ልሂድና አባቴን እቀብር ዘንድ ፍቀድልኝ አለ። ኢየሱስም። ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤ አንተስ ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ አለው። ፷፩ደግሞ ሌላው። ጌታ ሆይ፥ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን አስቀድሜ ከቤቴ ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ አለ። ፷፪ኢየሱስ ግን። ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም አለው።