፩ከዚህም በኋላ ጌታ ሌሎቹን ሰብዓ ሾመ፥ ሁለት ሁለትም አድርጎ እርሱ ሊሄድበት ወዳለው ከተማና ስፍራ ሁሉ በፊቱ ላካቸው። ፪አላቸውም። መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዴህ የመከሩን ጌታ ለመከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት። ፫ሂዱ፤ እነሆ፥ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ። ፬ኮረጆም ከረጢትም ጫማም አትያዙ፤ በመንገድም ለማንም እጅ አትንሡ። ፭ወደምትገቡበት ቤት ሁሉ አስቀድማችሁ። ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ። ፮በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር፥ ሰላማችሁ ያድርበታል፤ አለዚያም ይመለስላችኋል። ፯በዚያም ቤት ከእነርሱ ዘንድ ካለው እየበላችሁና እየጠጣችሁ ተቀመጡ፤ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋልና። ከቤት ወደ ቤት አትተላለፉ። ፰ወደምትገቡባትም ከተማ ሁሉ ቢቀበሉአችሁ፥ ያቀረቡላችሁን ብሉ፤ ፱በእርስዋም ያሉትን ድውዮችን ፈውሱና። የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ቀረበች በሉአቸው። ፲ነገር ግን ወደምትገቡባት ከተማ ሁሉ ባይቀበሉአችሁ፥ ወደ አደባባይዋ ወጥታችሁ። ፲፩ከከተማችሁ የተጣበቀብንን ትቢያ እንኳን እናራግፍላችኋለን፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ግን ወደ እናንተ እንደ ቀረበች ይህን እወቁ በሉ። ፲፪እላችኋለሁ፥ በዚያን ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶም ይቀልላታል። ፲፫ወዮልሽ ኮራዚን፥ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው በአመድም ተቀምጠው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበር። ፲፬ነገር ግን በፍርድ ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። ፲፭አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ። ፲፮የሚሰማችሁ እኔን ይሰማል፥ እናንተንም የጣለ እኔን ይጥላል፤ እኔንም የጣለ የላከኝን ይጥላል። ፲፯ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው። ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል አሉት። ፲፰እንዲህም አላቸው ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። ፲፱እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም። ፳ነገር ግን መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፥ ስማችሁ ግን በሰማያት ሰለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ። ፳፩በዚያን ሰዓት ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት አደረገና። የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግናለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና። ፳፪ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፥ ወልድንም ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፥ አብንም ማን እንደ ሆነ ከወልድ በቀር ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር የሚያውቅ የለም አለ። ፳፫ወደ ደቀ መዛሙርቱም ዘወር ብሎ ለብቻቸው። የምታዩትን የሚያዩ ዓይኖች ብፁዓን ናቸው። ፳፬እላችኋለሁና፥ እናንተ የምታዩትን ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት ሊያዩ ወደዱ አላዩምም፥ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ወድደው አልሰሙም አለ። ፳፭እነሆም፥ አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው ተነሥቶ። መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? አለው። ፳፮እርሱም በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ? አለው። ፳፯እርሱም መልሶ። ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው። ፳፰ኢየሱስም። እውነት መለስህ፤ ይህን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ አለው። ፳፱እርሱ ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ ኢየሱስን። ባልንጀራዬስ ማን ነው? አለው። ፴ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ። አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ። ፴፩ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። ፴፪እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። ፴፫አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት፥ ፴፬ቀርቦም ዘይትና የወይን ጠጅ በቍስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፥ በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማደርያ ወሰደው ጠበቀውም። ፴፭በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና። ጠብቀው፥ ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ አለው። ፴፮እንግዲህ ከነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመስልሃል? ፴፯እርሱም። ምሕረት ያደረገለት አለ። ኢየሱስም። ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ አለው። ፴፰ሲሄዱም እርሱ ወደ አንዲት መንደር ገባ፤ ማርታ የተባለች አንዲት ሴትም በቤትዋ ተቀበለችው። ፴፱ለእርስዋም ማርያም የምትባል እኅት ነበረቻት፥ እርስዋም ደግሞ ቃሉን ልትሰማ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጣ ነበረች። ፵ማርታ ግን አገልግሎት ስለ በዛባት ባከነች፤ ቀርባም። ጌታ ሆይ፥ እኔ እንድሠራ እኅቴ ብቻዬን ስትተወኝ አይገድህምን? እንኪያስ እንድታግዘኝ ንገራት አለችው። ፵፩ኢየሱስም መልሶ። ማርታ፥ ማርታ፥ በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፥ ፵፪የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም አላት።