፩እርሱም በአንድ ስፍራ ይጸልይ ነበር፥ በጨረሰም ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ። ጌታ ሆይ፥ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርቱን እንዳስተማረ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው። ፪አላቸውም። ስትጸልዩ እንዲህ በሉ። በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ ፫የዕለት እንጀራችንን ዕለት ዕለት ስጠን፤ ፬ኃጢአታችንንም ይቅር በለን፥ እኛ ደግሞ የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና፤ ከክፉ አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን። ፭እንዲህም አላቸው። ከእናንተ ማናቸውም ወዳጅ ያለው፥ በእኩል ሌሊትስ ወደ እርሱ ሄዶ። ወዳጄ ሆይ፥ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፥ ፮አንድ ወዳጄ ከመንገድ ወደ እኔ መጥቶ የማቀርብለት የለኝምና ይላልን? ፯ያም ከውስጥ መልሶ። አታድክመኝ፤ አሁን ደጁ ተቈልፎአል ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ አሉ፤ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም ይላልን? ፰እላችኋለሁ፥ ወዳጅ ስለ ሆነ ተነሥቶ ባይሰጠው እንኳ፥ ስለ ንዝነዛው ተነስቶ የሚፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል። ፱እኔም እላችኋለሁ። ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፍትላችሁማል። ፲የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልግም ያገኛል፥ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳው ይከፈትለታል። ፲፩አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ እርሱም ድንጋይ ይሰጠዋልን? ዓሣ ደግሞ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ ይሰጠዋልን? ፲፪ወይስ እንቍላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? ፲፫እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው? ፲፬ዲዳውንም ጋኔን ያወጣ ነበር፤ ጋኔኑም ከወጣ በኋላ ዲዳው ተናገረ ሕዝቡም ተደነቁ፤ ፲፭ነገር ግን ከእነርሱ አንዳንዱ። በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል አሉ። ፲፮ሌሎችም ሲፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ይፈልጉ ነበር። ፲፯እርሱ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው። እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁሉ ትጠፋለች፤ ቤትም በቤት ላይ ይወድቃል። ፲፰እኔ አጋንንትን በብዔል ዜቡል እንዳወጣ ትላላችሁና ሰይጣን ደግሞ እርስ በርሱ ከተለያየ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች? ፲፱እኔስ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ ልጆቻችሁ በማን ያወጡአቸዋል? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል። ፳እኔ ግን በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች። ፳፩ኃይለኛ ሰው ጋሻና ጦር ይዞ የራሱን ግቢ ቢጠብቅ፥ ያለው ገንዘቡ በሰላም ይሆናል፤ ፳፪ከእርሱ ይልቅ የሚበረታ መጥቶ ሲያሸንፈው ግን፥ ታምኖበት የነበረውን ጋሻና ጦር ይወስድበታል ምርኮውንም ያካፍላል። ፳፫ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፥ ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል። ፳፬ርኵስ መንፈስ ከሰው በወጣ ጊዜ ዕረፍትን እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፤ ባያገኝም። ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል፤ ፳፭ሲመጣም ተጠርጎ አጊጦም ያገኘዋል። ፳፮ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሌሎችን ሰባት አጋንንት ከእርሱ ጋር ይይዛል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል። ፳፯ይህንም ሲናገር፥ ከሕዝቡ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ። የተሸከመችህ ማኅፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው አለችው። ፳፰እርሱ ግን። አዎን፥ ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው አለ። ፳፱ብዙ ሕዝብም በተሰበሰቡ ጊዜ እንዲህ ይል ጀመር። ይህ ትውልድ ክፉ ነው፤ ምልክት ይፈልጋል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ፴ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደ ሆናቸው፥ እንዲሁ ደግሞ የሰው ልጅ ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናል። ፴፩ንግሥተ አዜብ በፍርድ ከዚህ ትውልድ ሰዎች ጋር ተነሥታ ትፈርድባቸዋለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፥ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ። ፴፪የነነዌ ሰዎች በፍርድ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ። ፴፫መብራትንም አብርቶ በስውር ወይም በእንቅብ በታች የሚያኖረው የለም፥ የሚገቡ ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል እንጂ። ፴፬የሰውነትህ መብራት ዓይንህ ናት። ዓይንህ ጤናማ በሆነች ጊዜ ሰውነትህ ሁሉ ደግሞ ብሩህ ይሆናል። ዓይንህ ታማሚ በሆነች ጊዜ ግን ሰውነትህ ደግሞ የጨለመ ይሆናል። ፴፭እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ እንዳይሆን ተመልከት። ፴፮እንግዲህ ሰውነትህ ሁሉ የጨለማ ቍራጭ የሌለበት ብሩህ ቢሆን፥ መብራት በደመቀ ብርሃን እንደሚያበራልህ በጭራሽ ብሩህ ይሆናል። ፴፯ይህንንም ሲናገር አንድ ፈሪሳዊ ከእርሱ ጋር ምሳ ይበላ ዘንድ ለመነው ገብቶም ተቀመጠ። ፴፰ከምሳም በፊት አስቀድሞ እንዳልታጠበ ባየው ጊዜ ፈሪሳዊው ተደነቀ። ፴፱ጌታም እንዲህ አለው። አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጠራላችሁ፥ ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበታል ፵እናንት ደንቆሮዎች፥ የውጭውን የፈጠረ የውስጡን ደግሞ አልፈጠረምን? ፵፩ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፥ እነሆም፥ ሁሉ ንጹሕ ይሆንላችኋል። ፵፪ነገር ግን እናንተ ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከጤና አዳም ከአትክልትም ሁሉ አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና እግዚአብሔርን መውደድ ስለምትተላለፉ፥ ወዮላችሁ፤ ነገር ግን ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉት ይገባችሁ ነበር። ፵፫እናንተ ፈሪሳውያን፥ በምኵራብ የከበሬታ ወንበር በገበያም ሰላምታ ስለምትወዱ፥ ወዮላችሁ። ፵፬እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ሰዎች ሳያውቁ በላዩ የሚሄዱበት የተሰወረ መቃብር ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ። ፵፭ከሕግ አዋቂዎችም አንዱ መልሶ። መምህር ሆይ፥ ይህን ማለትህ እኛን ደግሞ መስደብህ ነው አለው። ፵፮እርሱም እንዲህ አለ። እናንተ ደግሞ ሕግ አዋቂዎች፥ አስቸጋሪ ሸክም ለሰዎች ስለምታሸክሙ፥ ራሳችሁም በአንዲት ጣታችሁ ስንኳ ሸክሙን ስለማትነኩት፥ ወዮላችሁ። ፵፯አባቶቻችሁ የገደሉአቸውን የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ፥ ወዮላችሁ። ፵፰እንግዲህ ለአባቶቻችሁ ሥራ ትመሰክራላችሁ ትስማማላችሁም፤ እነርሱ ገድለዋቸዋልና፥ እናንተም መቃብራቸውን ትሠራላችሁ። ፵፱ስለዚህ ደግሞ የእግዚአብሔር ጥበብ እንዲህ አለች። ወደ እነርሱ ነቢያትንና ሐዋርያትን እልካለሁ፥ ከእነርሱም ይገድላሉ ያሳድዱማል፥ ፶ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የፈሰሰው የነቢያት ሁሉ ደም፥ ፶፩ከአቤል ደም ጀምሮ በመሠዊያውና በቤተ መቅደስ መካከል እስከ ጠፋው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ፥ ከዚህ ትውልድ እንዲፈለግ አዎን እላችኋለሁ፥ ከዚህ ትውልድ ይፈለጋል። ፶፪-፶፬እናንተ ሕግ አዋቂዎች፥ የእውቀትን መክፈቻ ስለ ወሰዳችሁ፥ ወዮላችሁ ራሳችሁ አልገባችሁም የሚገቡትንም ከለከላችሁ።