፩በዚያን ጊዜ የሕዝብ አእላፍ እርስ በርሳቸው እስኪረጋገጡ ድረስ ተሰብስበው ሳሉ፥ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ይል ጀመር። አስቀድማችሁ ከፈሪሳውያን እርሾ ተጠበቁ፥ እርሱም ግብዝነት ነው። ፪ነገር ግን የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለም። ፫ስለዚህ በጨለማ የምትናገሩት ሁሉ በብርሃን ይሰማል፥ በእልፍኝም ውስጥ በጆሮ የምትናገሩት በሰገነት ላይ ይሰበካል። ፬ለእናንተም ለወዳጆቼ እላችኋለሁ፥ ሥጋን የሚገድሉትን በኋላም አንድ ስንኳ የሚበልጥ ሊያደርጉ የማይችሉትን አትፍሩ። ፭እኔ ግን የምትፈሩትን አሳያችኋለሁ፤ ከገደለ በኋላ ወደ ገሃነም ለመጣል ሥልጣን ያለውን ፍሩ። አዎን እላችኋለሁ፥ እርሱን ፍሩ። ፮አምስት ድንቢጦች በአሥር ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ስንኳ በእግዚአብሔር ፊት አትረሳም። ፯ነገር ግን የእናንተ የራሳችሁ ጠጕር ሁሉ እንኳ የተቈጠረ ነው፤ እንግዲያስ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች ትበልጣላችሁ። ፰እላችሁማለሁ፥ በሰው ፊት የሚመሰክርልኝ ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይመሰክርለታል፤ ፱በሰውም ፊት የሚክደኝ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ይካዳል። ፲በሰው ልጅም ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ መንፈስ ቅዱስን የሚሰድብ ግን አይሰረይለትም። ፲፩ወደ ምኵራቦችና ወደ መኳንንቶችም ወደ ገዢዎችም ሲጐትቱአችሁ፥ እንዴት ወይም ምን እንድትመልሱ ወይም እንድትናገሩ አትጨነቁ፤ ፲፪መንፈስ ቅዱስ በዚያች ሰዓት ልትናገሩ የሚገባችሁን ያስተምራችኋልና። ፲፫ከሕዝቡም አንድ ሰው። መምህር ሆይ፥ ርስቱን ከእኔ ጋር እንዲካፈል ለወንድሜ ንገረው አለው። ፲፬እርሱም። አንተ ሰው፥ ፈራጅና አካፋይ በላያችሁ አንድሆን ማን ሾመኝ? አለው። ፲፭የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ አላቸው። ፲፮ምሳሌም ነገራቸው እንዲህ ሲል። አንድ ባለ ጠጋ ሰው እርሻ እጅግ ፍሬያም ሆነችለት። ፲፯እርሱም። ፍሬዬን የማከማችበት ስፍራ አጥቻለሁና ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ። ፲፰እንዲህ አደርጋለሁ፤ ጐተራዬን አፍርሼ ሌላ የሚበልጥ እሠራለሁ፥ በዚያም ፍሬዬንና በረከቴን ሁሉ አከማቻለሁ፤ ፲፱ነፍሴንም። አንቺ ነፍሴ፥ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፥ ብዪ፥ ጠጪ፥ ደስ ይበልሽ እላታለሁ አለ። ፳እግዚአብሔር ግን። አንተ ሰነፍ፥ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፤ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል? አለው። ፳፩ለራሱ ገንዘብ የሚያከማች፥ በእግዚአብሔር ዘንድም ባለ ጠጋ ያልሆነ እንዲህ ነው። ፳፪ለደቀ መዛሙርቱም እንዲህ አለ። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ለነፍሳችሁ በምትበሉት ወይም ለሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ። ፳፫ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልና። ፳፬ቍራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም፥ ዕቃ ቤትም ወይም ጎተራ የላቸውም፥ እግዚአብሔርም ይመግባቸዋል፤ እናንተስ ከወፎች እንዴት ትበልጣላችሁ? ፳፭ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? ፳፮እንግዲህ ትንሹን ነገር ስንኳ የማትችሉ ከሆናችሁ፥ ስለ ምን በሌላ ትጨነቃላችሁ? ፳፯አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዲቱ አለበሰም። ፳፰እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን በሜዳ የሆነውን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? ፳፱እናንተም የምትበሉትን የምትጠጡትንም አትፈልጉ፥ አታወላውሉም፤ ፴ይህንስ ሁሉ በዓለም ያሉ አሕዛብ ይፈልጉታልና፤ የእናንተም አባት ይህ እንዲያስፈልጋችሁ ያውቃል። ፴፩ዳሩ ግን መንግሥቱን ፈልጉ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ፴፪አንተ ታናሽ መንጋ፥ መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። ፴፫ያላችሁን ሽጡ ምጽዋትም ስጡ፤ ሌባ በማይቀርብበት ብልም በማያጠፋበት በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን የማያረጁትንም ኮረጆዎች ለራሳችሁ አድርጉ፤ ፴፬መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናልና። ፴፭ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤ ፴፮እናንተም ጌታቸው መጥቶ ደጁን ሲያንኳኳ ወዲያው እንዲከፍቱለት ከሰርግ እስኪመለስ ድረስ የሚጠብቁ ሰዎችን ምሰሉ ፴፯ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ታጥቆ በማዕድ ያስቀምጣቸዋል ቀርቦም ያገለግላቸዋል። ፴፰ከሌሊቱም በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንዲሁ ቢያገኛቸው፥ እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው። ፴፱ይህን ግን እወቁ ባለቤት በምን ሰዓት ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ፥ ቤቱም እንዲቆፈር ባልፈቀደም ነበር። ፵እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና። ፵፩ጴጥሮስም። ጌታ ሆይ፥ ይህን ምሳሌ ለእኛ ወይስ ደግሞ ለሁሉ ትናገራለህን? አለው። ፵፪ጌታም አለ። እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ልባም መጋቢ ማን ነው? ፵፫ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው። ፵፬እውነት እላችኋለሁ፥ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ፵፭ያ ባሪያ ግን። ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ ሎሌዎችንና ገረዶችንም ይመታ ይበላም ይጠጣም ይሰክርም ዘንድ ቢጀምር፥ ፵፮የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፥ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል እድሉንም ከማይታመኑ ጋር ያደርጋል። ፵፯የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደ ፈቃዱም ያላደረገ ያ ባሪያ እጅግ ይገረፋል፤ ፵፰ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል። ፵፱በምድር ላይ እሳት ልጥል መጣሁ፥ አሁንም የነደደ ከሆነ ዘንድ ምን እፈልጋለሁ? ፶ነገር ግን የምጠመቃት ጥምቀት አለችኝ፥ እስክትፈጸምም ድረስ እንዴት እጨነቃለሁ? ፶፩በምድር ላይ ሰላምንም ለመስጠት የመጣሁ ይመስላችኋልን? እላችኋለሁ፥ አይደለም፥ መለያየትን እንጂ። ፶፪ከአሁን ጀምሮ በአንዲት ቤት አምስት ሰዎች ይኖራሉና፤ ሦስቱም በሁለቱ ላይ ሁለቱም በሦስቱ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ። ፶፫አባት በልጁ ላይ ልጅም በአባቱ ላይ፥ እናት በልጅዋ ላይ ልጅዋም በእናትዋ ላይ፥ አማት በምራትዋ ላይ ምራትም በአማትዋ ላይ ተነሥተው ይለያያሉ። ፶፬ደግሞም ሕዝቡን እንዲህ አለ። ደመና ከምዕራብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ፥ ወዲያው። ዝናብ ይመጣል ትላላችሁ፥ እንዲሁም ይሆናል፤ ፶፭በአዜብም ነፋስ ሲነፍስ። ትኩሳት ይሆናል ትላላችሁ፥ ይሆንማል። ፶፮እናንት ግብዞች፥ የምድሩንና የሰማዩን ፊት ልትመረምሩ ታውቃላችሁ፥ ነገር ግን ይህን ዘመን የማትመረምሩ እንዴት ነው? ፶፯ራሳችሁ ደግሞ ጽድቅን የማትፈርዱ ስለ ምን ነው? ፶፰ከባላጋራህ ጋር ወደ ሹም ብትሄድ፥ ወደ ዳኛ እንዳይጐትትህ ዳኛውም ለሎሌው አሳልፎ እንዳይሰጥህ ሎሌውም በወኅኒ እንዳይጥልህ፥ ገና በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ እንድትታረቅ ትጋ። ፶፱እልሃለሁ፥ የመጨረሻዋን ግማሽ ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ ከቶ አትወጣም።