፩በሰንበትም ከፈሪሳውያን አለቆች ወደ አንዱ ቤት እንጀራ ሊበላ በገባ ጊዜ እነርሱ ይጠባበቁት ነበር። ፪እነሆም፥ ሆዱ የተነፋ ሰው በፊቱ ነበረ። ፫ኢየሱስም መልሶ። በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? ብሎ ለሕግ አዋቂዎችና ለፈሪሳውያን ተናገረ። ፬እነርሱ ግን ዝም አሉ። ይዞም ፈወሰውና አሰናበተው። ፭ከእናንተ አህያው ወይስ በሬው በጕድጓድ ቢወድቅ በሰንበት ወዲያው የማያወጣው ማን ነው? አላቸው። ፮ስለዚህ ነገርም ሊመልሱለት አልተቻላቸውም። ፯የታደሙትንም የከበሬታ ስፍራ እንደ መረጡ ተመልክቶ ምሳሌ ነገራቸው እንዲህ ሲል። ፰ማንም ለሰርግ ቢጠራህ በከበሬታ ስፍራ አትቀመጥ፤ ምናልባት ከአንተ ይልቅ የከበረ ተጠርቶ ይሆናልና አንተን እርሱንም የጠራ መጥቶ። ፱ለዚህ ስፍራ ተውለት ይልሃል፥ በዚያን ጊዜም እያፈርህ በዝቅተኛው ስፍራ ልትሆን ትጀምራለህ። ፲ነገር ግን በተጠራህ ጊዜ፥ የጠራህ መጥቶ። ወዳጄ ሆይ፥ ወደ ላይ ውጣ እንዲልህ፥ ሄደህ በዝቅተኛው ስፍራ ተቀመጥ፤ ያን ጊዜም ከአንተ ጋር በተቀመጡት ሁሉ ፊት ክብር ይሆንልሃል። ፲፩ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍ ይላል። ፲፪የጠራውንም ደግሞ እንዲህ አለው። ምሳ ወይም እራት ባደረግህ ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ በተራቸው ምናልባት እንዳይጠሩህ ብድራትም እንዳይመልሱልህ፥ ወዳጆችህንና ወንድሞችህን ዘመዶችህንም ባለ ጠጎች ጎረቤቶችህንም አትጥራ። ፲፫ነገር ግን ግብዣ ባደረግህ ጊዜ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንም ዕውሮችንም ጥራ፤ ፲፬የሚመልሱት ብድራት የላቸውምና ብፁዕ ትሆናለህ፤ በጻድቃን ትንሣኤ ይመለስልሃልና። ፲፭ከተቀመጡትም አንዱ ይህን ሰምቶ። በእግዚአብሔር መንግሥት እንጀራ የሚበላ ብፁዕ ነው አለው። ፲፮እርሱ ግን እንዲህ አለው። አንድ ሰው ታላቅ እራት አድርጎ ብዙዎችን ጠራ፤ ፲፯በእራትም ሰዓት የታደሙትን። አሁን ተዘጋጅቶአልና ኑ እንዲላቸው ባሪያውን ላከ። ፲፰ሁላቸውም በአንድነት ያመካኙ ጀመር። የፊተኛው። መሬት ገዝቼአለሁ ወጥቼም ላየው በግድ ያስፈልገኛል፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው። ፲፱ሌላውም። አምስት ጥምድ በሬዎች ገዝቼአለሁ ልፈትናቸውም እሄዳለሁ፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው። ፳ሌላውም። ሚስት አግብቼአለሁ ስለዚህም ልመጣ አልችልም አለው። ፳፩ባሪያውም ደርሶ ይህን ለጌታው ነገረው። በዚያን ጊዜ ባለቤቱ ተቆጥቶ ባሪያውን። ወደ ከተማ ጎዳናና ወደ ስላች ፈጥነህ ውጣ ድሆችንና ጕንድሾችን አንካሶችንና ዕውሮችንም ወደዚህ አግባ አለው። ፳፪ባሪያውም። ጌታ ሆይ፥ እንዳዘዝኸኝ ተደርጎአል፥ ገናም ስፍራ አለ አለው። ፳፫ጌታውም ባሪያውን። ቤቴ እንዲሞላ ወደ መንገድና ወደ ቅጥር ውጣና ይገቡ ዘንድ ግድ በላቸው፤ ፳፬እላችኋለሁና፥ ከታደሙት ከእነዚያ ሰዎች አንድ ስንኳ እራቴን አይቀምስም አለው። ፳፭ብዙም ሕዝብ ከእርሱ ጋር ይሄዱ ነበር፥ ዘወር ብሎም እንዲህ አላቸው። ፳፮ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። ፳፯ማንም መስቀሉን ተሸክሞ በኋላዬ የማይመጣ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። ፳፰ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ ከሳራውን የማይቈጥር ማን ነው? ፳፱ያለዚያ መሠረቱን ቢመሠርት፥ ሊደመድመውም ቢያቅተው፥ ያዩት ሁሉ። ፴ይህ ሰው ሊሠራ ጀምሮ ሊደመድመው አቃተው ብለው ሊዘብቱበት ይጀምራሉ። ፴፩ወይም ሌላውን ንጉሥ በጦርነት ሊጋጠም የሚሄድ፥ ከሁለት እልፍ ጋር የሚመጣበትን በአንድ እልፍ ሊገናኝ የሚችል እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ የማያስብ ንጉሥ ማን ነው? ፴፪ባይሆንስ ሌላው ገና ሩቅ ሳለ መልክተኞች ልኮ ዕርቅ ይለምናል። ፴፫እንግዲህ እንደዚሁ ማንም ከእናንተ ያለውን ሁሉ የማይተው ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም። ፴፬ጨው መልካም ነው፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፈጣል? ፴፭ለምድር ቢሆን ለፍግ መቈለያም ቢሆን አይረባም፤ ወደ ውጭ ይጥሉታል። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።