፩ቀራጮችና ኃጢአተኞችም ሁሉ ሊሰሙት ወደ እርሱ ይቀርቡ ነበር። ፪ፈሪሳውያንና ጻፎችም። ይህስ ኃጢአተኞችን ይቀበላል ከእነርሱም ጋር ይበላል ብለው እርስ በርሳቸው አንጐራጐሩ። ፫ይህንም ምሳሌ ነገራቸው እንዲህ ሲል። ፬መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማን ነው? ፭ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፤ ፮ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ። የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል። ፯እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል። ፰ወይም አሥር ድሪም ያላት አንድ ድሪም ቢጠፋባት፥ መብራት አብርታ ቤትዋንም ጠርጋ እስክታገኘው ድረስ አጥብቃ የማትፈልግ ሴት ማን ናት? ፱ባገኘችውም ጊዜ ወዳጆችዋንና ጐረቤቶችዋን በአንድነት ጠርታ። የጠፋውን ድሪሜን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ትላቸዋለች። ፲እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል። ፲፩እንዲህም አለ። አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ፲፪ከእነርሱም ታናሹ አባቱን። አባቴ ሆይ፥ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው። ፲፫ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፥ ከዚያም እያባከነ ገዘቡን በተነ። ፲፬ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፥ እርሱም ይጨነቅ ጀመር። ፲፭ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፥ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው። ፲፮እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፥ የሚሰጠውም አልነበረም። ፲፯ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ። እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። ፲፰ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና። አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ፲፱ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ። ፳ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ። እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው። ፳፩ልጁም። አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም አለው። ፳፪አባቱ ግን ባሪያዎቹን አለ። ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፥ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ፤ ፳፫የሰባውን ፊሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፥ እንብላም ደስም ይበለን፤ ፳፬ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም። ደስም ይላቸው ጀመር። ፳፭ታላቁ ልጁ በእርሻ ነበረ፤ መጥቶም ወደ ቤት በቀረበ ጊዜ የመሰንቆና የዘፈን ድምፅ ሰማ፤ ፳፮ከብላቴናዎችም አንዱን ጠርቶ። ይህ ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀ። ፳፯እርሱም። ወንድምህ መጥቶአልና በደኅና ስላገኘው አባትህ የሰባውን ፊሪዳ አረደለት አለው። ፳፰ተቈጣም ሊገባም አልወደደም፤ አባቱም ወጥቶ ለመነው። ፳፱እርሱ ግን መልሶ አባቱን። እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት እንደ ባሪያ ተገዝቼልሃለሁ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ ለእኔም ከወዳጆቼ ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ ጥቦት ስንኳ አልሰጠኸኝም፤ ፴ነገር ግን ገንዘብህን ከጋለሞቶች ጋር በልቶ ይህ ልጅህ በመጣ ጊዜ፥ የሰባውን ፊሪዳ አረድህለት አለው። ፴፩እርሱ ግን። ልጄ ሆይ፥ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፥ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ ፴፪ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል አለው።