፩-፫ኢየሱስንም የትኛው እንደ ሆነ ሊያይ ይፈልግ ነበር፤ ቁመቱም አጭር ነበረና ስለ ሕዝቡ ብዛት አቃተው። በዚያችም መንገድ ያልፍ ዘንድ አለውና ያየው ዘንድ ወደ ፊት ሮጦ በአንድ ሾላ ላይ ወጣ። ኢየሱስም ወደዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ፥ አሻቅቦ አየና። ዘኬዎስ ሆይ፥ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ አለው። ፈጥኖም ወረደ በደስታም ተቀበለው። ሁሉም አይተው። ከኃጢአተኛ ሰው ጋር ሊውል ገባ ብለው አንጐራጐሩ። ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን። ጌታ ሆይ፥ ካለኝ ሁሉ እኵሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደ ሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ አለው። ኢየሱስም። እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል፤ የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና አለው። ፲፩እነርሱም ይህን ሲሰሙ፥ ወደ ኢየሩሳሌም መቅረቡ ስለ ሆነ የእግዚአብሔርም መንግሥት ፈጥኖ ሊገለጥ እንዳለው ስለ መሰላቸው ምሳሌ ጭምር ተናገረ። ፲፪ስለዚህም እንዲህ አላቸው። አንድ መኰንን ለራሱ መንግሥትን ይዞ ሊመለሰ ወደ ሩቅ አገር ሄደ። ፲፫አሥር ባሪያዎችንም ጠርቶ አሥር ምናን ሰጣቸውና። እስክመጣ ድረስ ነግዱ አላቸው። ፲፬የአገሩ ሰዎች ግን ይጠሉት ነበርና። ይህ በላያችን ሊነግሥ አንወድም ብለው በኋላው መልክተኞችን ላኩ። ፲፭መንግሥትንም ይዞ በተመለሰ ጊዜ፥ ገንዘብ የሰጣቸውን እነዚህን ባሪያዎች ነግደው ምን ያህል እንዳተረፉ ያውቅ ዘንድ እንዲጠሩለት አዘዘ። ፲፮የፊተኛውም ደርሶ። ጌታ ሆይ፥ ምናንህ አሥር ምናን አተረፈ አለው። ፲፯እርሱም። መልካም፥ አንተ በጎ ባሪያ፥ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በአሥር ከተማዎች ላይ ሥልጣን ይሁንልህ አለው። ፲፰ሁለተኛውም መጥቶ። ጌታ ሆይ፥ ምናንህ አምስት ምናን አተረፈ አለው። ፲፱ይህንም ደግሞ። አንተም በአምስት ከተማዎች ላይ ሁን አለው። ሌላውም መጥቶ። ጌታ ሆይ፥ በጨርቅ ጠቅልዬ የጠበቅኋት ምናንህ እነሆ፤ ፳፩ፈርቼሃለሁና፥ ጨካኝ ሰው ስለ ሆንህ፤ ያላኖርኸውን ትወስዳለህ ያልዘራኸውንም ታጭዳለህ አለው። ፳፪እርሱም። አንተ ክፉ ባሪያ፥ አፍህ በተናገረው እፈርድብሃለሁ። እኔ ያላኖርሁትን የምወስድና ያልዘራሁትን የማጭድ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ አወቅህ፤ ምን ነው ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ያልሰጠኸው? ፳፫እኔም መጥቼ ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር አለው። ፳፬በዚያም ቆመው የነበሩትን። ምናኑን ውሰዱበት አሥሩ ምናን ላለውም ስጡት አላቸው። ፳፭እነርሱም። ጌታ ሆይ፥ አሥር ምናን አለው አሉት። ፳፮እላችኋለሁ፥ ላለው ሁሉ ይሰጠዋል፥ ከሌለው ግን ያው ያለው ስንኳ ይወሰድበታል። ፳፯ነገር ግን እነዚያን በላያቸው ልነግሥ ያልወደዱትን ጠላቶቼን ወደዚህ አምጡአቸው በፊቴም እረዱአቸው። ፳፰ይህንም ከተናገረ በኋላ፥ ወደ ኢየሩሳሌም ሲወጣ ይቀድማቸው ነበር። ፳፱ደብረ ዘይትም በሚባል ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከና። በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ ወደ እርስዋም ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፥ ፈትታችሁም አምጡት። ፴፩ማንም። ስለ ምን ትፈቱታላችሁ? ብሎ ቢጠይቃችሁ፥ እንዲሁ። ለጌታ ያስፈልገዋል በሉ አላቸው። ፴፪የተላኩትም ሄደው እንዳላቸው አገኙ። ፴፫እነርሱም ውርንጫውን ሲፈቱ ጌቶቹ። ውርንጫውን ስለ ምን ትፈቱታላችሁ? አሉአቸውም ፴፬እነርሱም። ለጌታ ያስፈልገዋል አሉ። ፴፭ወደ ኢየሱስም አመጡት፥ በውርንጫውም ላይ ልብሳቸውን ጭነው ኢየሱስን አስቀመጡት። ፴፮ሲሄድም ልብሳቸውን በመንገድ ያነጥፉ ነበር። ፴፯ወደ ደብረ ዘይት ቍልቍለትም አሁን በቀረበ ጊዜ፥ ደቀ መዛሙርቱ ሁላቸው ደስ እያላቸው ተአምራትን ሁሉ ስላዩ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን ሊያመሰግኑ ጀምረው። ፴፰በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው፤ በሰማይ ሰላም በአርያምም ክብር አሉ። ፴፱ከሕዝብም መካከል ከፈሪሳውያን አንዳንዱ። መምህር ሆይ፥ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት። መልሶም። እላችኋለሁ፥ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ አላቸው። ፵፩ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፥ ፵፪እንዲህ እያለ። ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ፤ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሮአል። ፵፫ወራት ይመጣብሻልና፥ ጠላቶችሽም ቅጥር ይቀጥሩብሻል ይከቡሻልም በየበኵሉም ያስጨንቁሻል፤ ፵፬አንቺንም በአንቺም ውስጥ የሚኖሩትን ልጆችሽን ወደ ታች ይጥላሉ፥ በአንቺ ውስጥም ድንጋይ በድንጋይ ላይ አይተዉም፥ የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና። ፵፭ወደ መቅደስም ገብቶ በእርሱ የሚሸጡትን የሚገዙትንም ያወጣ ጀመር፤ ፵፮እርሱም። ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት አላቸው። ፵፯ዕለት ዕለትም በመቅደስ ያስተምር ነበር፤ ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች የሕዝቡ ታላላቆችም ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፥ ፵፰የሚያደርጉበትንም አጡ፤ ሕዝቡ ሁሉ ሲሰሙት ተንጠልጥለውበት ነበርና።