አንድ ቀንም ሕዝቡን በመቅደስ ሲያስተምር ወንጌልንም ሲሰብክላቸው፥ የካህናት አለቆችና ጻፎች ከሽማግሌዎች ጋር ወደ እርሱ ቀረቡና። እስኪ ንገረን፤ እነዚህን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ ወይስ ይህን ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው? ብለው ተናገሩት። መልሶም። እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፥ እናንተም ንገሩኝ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? አላቸው። እርስ በርሳቸውም ሲነጋገሩ። ከሰማይ ብንል። ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ ከሰው ብንል ግን ሕዝቡ ሁሉ ይወግሩናል፤ ዮሐንስ ነቢይ እንደ ነበረ ሁሉ ያምኑ ነበርና አሉ። መልሰውም። ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም አሉት። ኢየሱስም። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው። ይህንም ምሳሌ ለሕዝቡ ይላቸው ጀመር። አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ ለገበሬዎችም አከራይቶ ለብዙ ዘመን ወደ ሌላ አገር ሄደ። በጊዜውም ከወይኑ አትክልት ፍሬ እንዲሰጡት አንድ ባሪያ ወደ ገበሬዎች ላከ፤ ገበሬዎቹ ግን ደበደቡት ባዶውንም ሰደዱት። ፲፩ጨምሮም ሌላውን ባሪያ ላከ፤ እነርሱም ያን ደግሞ ደበደቡት አዋርደውም ባዶውን ሰደዱት። ፲፪ጨምሮም ሦስተኛውን ላከ፤ እነርሱም ይህን ደግሞ አቍሰለው አወጡት። ፲፫የወይኑም አትክልት ጌታ። ምን ላድርግ? የምወደውን ልጄን እልካለሁ፤ ምናልባት እርሱን አይተው ያፍሩታል አለ። ፲፬ገበሬዎቹ ግን አይተውት እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ። ወራሹ ይህ ነው፤ ርስቱ ለእኛ እንዲሆን ኑ እንግደለው አሉ። ፲፭ከወይኑም አትክልት ወደ ውጭ አውጥተው ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ ምን ያደርጋቸዋል? ፲፮ይመጣል እነዚህንም ገበሬዎች ያጠፋል፥ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል። ይህንም በሰሙ ጊዜ። ይህስ አይሁን አሉ። ፲፯እርሱ ግን ወደ እነርሱ ተመልክቶ። እንግዲህ። ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ ተብሎ የተጻፈው ይህ ምንድር ነው? ፲፰በዚያም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ሁሉ ይቀጠቀጣል፤ የሚወድቅበትን ሁሉ ግን ይፈጨዋል አለ። ፲፱የካህናት አለቆችና ጻፎችም ይህን ምሳሌ በእነርሱ ላይ እንደ ተናገረ አውቀው በዚያች ሰዓት እጃቸውን ሊጭኑበት ፈለጉ ነገር ግን ሕዝቡን ፈሩ። ሲጠባበቁም ወደ ገዢ ግዛትና ሥልጣን አሳልፈው እንዲሰጡት ጻድቃን መስለው በቃሉ የሚያጠምዱትን ሸማቂዎች ሰደዱበት። ፳፩ጠይቀውም። መምህር ሆይ፥ እውነትን እንድትናገርና እንድታስተምር ለሰው ፊትም እንዳታደላ እናውቃለን፥ በእውነት የእግዚአብሔርን መንገድ ታስተምራለህ እንጂ፤ ፳፪ለቄሣር ግብር ልንሰጥ ተፈቅዶአልን? ወይስ አልተፈቀደም? አሉት። ፳፫እርሱ ግን ተንኰላቸውንም ተመልክቶ። ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ? አንድ ዲናር አሳዩኝ፤ ፳፬መልኩ ጽሕፈቱስ የማን ነው? አላቸው። መልሰውም። የቄሣር ነው አሉት። ፳፭እርሱም። እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው። ፳፮በሕዝቡም ፊት በቃሉ ሊያጠምዱት አልቻሉም በመልሱም እየተደነቁ ዝም አሉ። ፳፯ትንሣኤ ሙታንንም የሚክዱ ከሰዱቃውያን አንዳንዶቹ ቀርበው ጠየቁት፥ ፳፰እንዲህ ሲሉ። መምህር ሆይ፥ ሙሴ። ሚስት ያለችው የአንድ ሰው ወንድም ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፥ ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ ብሎ ጻፈልን። ፳፱እንግዲያስ ሰባት ወንድማማች ነበሩ፤ የፊተኛውም ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ሞተ፤ ፴-፴፪ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ደግሞ ሞተች። ፴፫እንግዲህ ሰባቱ አግብተዋታልና ሴቲቱ በትንሣኤ ከእነርሱ ለማንኛቸው ሚስት ትሆናለች? ፴፬ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። የዚህ ዓለም ልጆች ያገባሉ ይጋባሉም፥ ፴፭ያን ዓለምና ከሙታን ትንሣኤ ሊያገኙ የሚገባቸው እነዚያ ግን አያገቡም አይጋቡምም፥ እንደ መላእክት ናቸውና፥ ፴፮ሊሞቱም ወደ ፊት አይቻላቸውም፥ የትንሣኤም ልጆች ስለ ሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ፴፯ሙታን እንዲነሡ ግን ሙሴ ደግሞ በቍጥቋጦው ዘንድ ጌታን የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ በማለቱ አስታወቀ፤ ፴፰ሁሉ ለእርሱ ሕያዋን ስለ ሆኑ፥ የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። ፴፱ከጻፎችም አንዳንዶቹ መልሰው። መምህር ሆይ፥ መልካም ተናገርህ አሉት። ወደ ፊትም አንድ ነገር ስንኳ ሊጠይቁት አልደፈሩም። ፵፩እንዲህም አላቸው። ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው እንዴት ይላሉ? ፵፪-፵፬እንግዲህ ዳዊት። ጌታ ብሎ ይጠራዋል፥ እንዴትስ ልጁ ይሆናል? ፵፭ሕዝቡም ሁሉ ሲሰሙ ደቀ መዛሙርቱን። ፵፮ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞር ከሚፈልጉ፥ በገበያም ሰላምታ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥ በምሳም የከበሬታ ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ፤ ፵፯የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ፥ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ አለ።