በእምነት የደከመውንም ተቀበሉት፥ በአሳቡም ላይ አትፍረዱ። ሁሉን ይበላ ዘንድ እንደ ተፈቀደለት የሚያምን አለ፥ ደካማው ግን አትክልት ይበላል። የሚበላ የማይበላውን አይናቀው የማይበላውም በሚበላው አይፍረድ፥ እግዚአብሔር ተቀብሎታልና። አንተ በሌላው ሎሌ የምትፈርድ ማን ነህ? እርሱ ቢቆም ወይም ቢወድቅ ለገዛ ጌታው ነው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሊያቆመው ይችላልና ይቆማል። ይህ ሰው አንድ ቀን ከሌላ ቀን እንዲሻል ያስባል፥ ያ ግን ቀን ሁሉ አንድ እንደ ሆነ ያስባል፤ እያንዳንዱ በገዛ አእምሮው አጥብቆ ይረዳ። ቀንን የሚያከብር ለጌታ ብሎ ያከብራል፤ የሚበላም እግዚአብሔርን ያመሰግናልና ለጌታ ብሎ ይበላል፤ የማይበላም ለጌታ ብሎ አይበላም እግዚአብሔርንም ያመሰግናል። ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና፥ ለራሱም የሚሞት የለም፤ በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፥ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን። ስለዚህ ነገር ሙታንንም ሕያዋንንም ይገዛ ዘንድ ክርስቶስ ሞቶአልና ሕያውም ሆኖአልና። አንተም በወንድምህ ላይ ስለ ምን ትፈርዳለህ? ወይስ አንተ ደግሞ ወንድምህን ስለ ምን ትንቃለህ? ሁላችን በክርስቶስ ፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለንና። ፲፩እኔ ሕያው ነኝ፥ ይላል ጌታ፥ ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል መላስም ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናል ተብሎ ተጽፎአልና። ፲፪እንግዲያስ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን። ፲፫እንግዲህ ከዛሬ ጀምሮ እርስ በርሳችን አንፈራረድ፤ ይልቁን ግን ለወንድም እንቅፋትን ወይም ማሰናከያን ማንም እንዳያኖርበት ይህን ቍረጡ። ፲፬በራሱ ርኵስ የሆነ ነገር እንደ ሌለ በጌታ በኢየሱስ ሆኜ አውቄአለሁ ተረድቼአለሁም፤ ነገር ግን ምንም ርኵስ እንዲሆን ለሚቆጥር ለእርሱ ርኵስ ነው። ፲፭ወንድምህንም በመብል ምክንያት የምታሳዝን ከሆንህ እንግዲህ በፍቅር አልተመላለስህም። ክርስቶስ ስለ እርሱ የሞተለትን እርሱን በመብልህ አታጥፋው። ፲፮እንግዲህ ለእናንተ ያለው መልካም ነገር አይሰደብ፤ ፲፯የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና። ፲፰እንደዚህ አድርጎ ለክርስቶስ የሚገዛ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛልና፥ በሰውም ዘንድ የተመሰገነ ነው። ፲፱እንግዲያስ ሰላም የሚቆምበትን እርስ በርሳችንም የምንታነጽበትን እንከተል። በመብል ምክንያት የእግዚአብሔርን ሥራ አታፍርስ። ሁሉ ንጹሕ ነው፥ በመጠራጠር የተበላ እንደ ሆነ ግን ለዚያ ሰው ክፉ ነው። ፳፩ሥጋን አለመብላት ወይንንም አለመጠጣት ወንድምህም የሚሰናከልበትን አለማድረግ መልካም ነው። ፳፪ለአንተ ያለህ እምነት በእግዚአብሔር ፊት ለራስህ ይሁንልህ። ፈትኖ መልካም እንዲሆን በሚቈጥረው ነገር በራሱ ላይ የማይፈርድ ብፁዕ ነው። ፳፫የሚጠራጠረው ግን ቢበላ በእምነት ስላልሆነ ተኮንኖአል፤ በእምነትም ያልሆነ ሁሉ ኃጢአት ነው።