፩በክንክራኦስ ባለች ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የምትሆን እኅታችንን ፌቤንን አደራ ብያችኋለሁ፤ ፪ለቅዱሳን እንደሚገባ በጌታ ተቀበሉአት፥ እርስዋ ለብዙዎች ለእኔም ለራሴ ደጋፊ ነበረችና፥ ከእናንተም በምትፈልገው በማናቸውም ነገር እርዱአት። ፫በክርስቶስ ኢየሱስ አብረውኝ ለሚሠሩ ለጵርስቅላና ለአቂላ ሰላምታ አቅርቡልኝ፤ ፬እነርሱም ስለ ነፍሴ ነፍሳቸውን ለሞት አቀረቡ፥ የአሕዛብም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የሚያመሰግኑአቸው ናቸው እንጂ እኔ ብቻ አይደለሁም፤ ፭በቤታቸውም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከእስያ ለክርስቶስ በኵራት ለሆነው ለምወደው ለአጤኔጦን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ፮ስለ እናንተ ብዙ ለደከመች ለማርያ ሰላምታ አቅርቡልኝ። ፯በሐዋርያት መካከል ስመ ጥሩዎች ለሆኑ፥ ደግሞም ክርስቶስን በማመን ለቀደሙኝ፥ አብረውኝም ለታሰሩ ለዘመዶቼ ለአንዲራኒቆንና ለዩልያን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ፰በጌታ ለምወደው ለጵልያጦን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ፱በክርስቶስ አብሮን ለሚሠራ ለኢሩባኖን ለምወደውም ለስንጣክን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ፲በክርስቶስ መሆኑ ተፈትኖ ለተመሰገነው ለኤጤሌን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከአርስጣባሉ ቤተ ሰዎች ላሉት ሰላምታ አቅርቡልኝ። ፲፩ለዘመዴ ለሄሮድዮና ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከንርቀሱ ቤተ ሰዎች በጌታ ላሉት ሰላምታ አቅርቡልኝ። ፲፪በጌታ ሆነው ለሚደክሙ ለፕሮፊሞናና ለጢሮፊሞሳ ሰላምታ አቅርቡልኝ። በጌታ እጅግ ለደከመች ለተወደደች ለጠርሲዳ ሰላምታ አቅርቡልኝ። ፲፫በጌታ ሆኖ ለታወቀ ለሩፎን ለእኔና ለእርሱም እናት ሰላምታ አቅርቡልኝ። ፲፬ለአስቀሪጦንና ለአፍለሶንጳ ለሄሮሜንም ለጳጥሮባም ለሄርማንም ከእነርሱም ጋር ላሉ ወንድሞች ሰላምታ አቅርቡልኝ። ፲፭ለፍሌጎንና ለዩልያ ለኔርያና ለእኅቱም ለአልንጦንም ከእነርሱ ጋር ላሉ ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ አቅርቡልኝ። ፲፮በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ። የክርስቶስ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ፲፯ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፥ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ፤ ፲፰እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፥ በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ። ፲፱መታዘዛችሁ ለሁሉ ተወርቶአልና፤ እንግዲህ በእናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ለበጎ ነገር ጥበበኞች ለክፉም የዋሆች እንድትሆኑ እወዳለሁ። ፳የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። ፳፩አብሮኝ የሚሠራ ጢሞቴዎስ ዘመዶቼም ሉቂዮስና ኢያሶን ሱሲጴጥሮስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ፳፪ይህን መልእክት የጻፍሁ እኔ ጤርጥዮስ በጌታ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ። ፳፫የእኔና የቤተ ክርስቲያን ሁሉ አስተናጋጅ ጋይዮስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። የከተማው መጋቢ ኤርስጦስ ወንድማችንም ቁአስጥሮስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ፳፬የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። ፳፭-፳፯ብቻውን ጥበብ ላለው ለእግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።