እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ፤ በእርሱም ደግሞ ወደ ቆምንበት ወደዚህ ጸጋ በእምነት መግባትን አግኝተናል፤ በእግዚአብሔር ክብርም ተስፋ እንመካለን። ፫-፭በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም። ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና። ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን። ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤ ፲፩ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን አሁን መታረቁን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን። ፲፪ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤ ፲፫ሕግ እስከ መጣ ድረስ ኃጢአት በዓለም ነበረና ነገር ግን ሕግ በሌለበት ጊዜ ኃጢአት አይቈጠርም፤ ፲፬ነገር ግን በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ፥ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው ለእርሱ አምሳሉ ነውና። ፲፭ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን እንደዚያው አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ሞተዋልና፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የሆነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዛ። ፲፮አንድ ሰውም ኃጢአትን በማድረጉ እንደ ሆነው መጠን እንደዚያው ስጦታው አይደለም፤ ፍርድ ከአንድ ሰው ለኵነኔ መጥቶአልና፥ ስጦታው ግን በብዙ በደል ለማጽደቅ መጣ። ፲፯በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ። ፲፰እንግዲህ በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኵነኔ ወደ ሰው ሁሉ እንደ መጣ፥ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ ምክንያት ስጦታው ሕይወትን ለማጽደቅ ወደ ሰው ሁሉ መጣ። ፲፱-፳፩በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።