፩በዚህም ወራት ደቀ መዛሙርት እየበዙ ሲሄዱ ከግሪክ አገር መጥተው የነበሩት አይሁድ በይሁዳ ኖረው በነበሩት አይሁድ አንጐራጐሩባቸው፥ በየቀኑ በተሠራው አገልግሎት መበለቶቻቸውን ችላ ይሉባቸው ነበርና። ፪አሥራ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሁሉን ጠርተው እንዲህ አሉአቸው። የእግዚአብሔር ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ ነገር አይደለም። ፫ወንድሞች ሆይ፥ በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፥ ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን፤ ፬እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን። ፭ይህም ቃል ሕዝብን ሁሉ ደስ አሰኛቸው፤ እምነትና መንፈስ ቅዱስም የሞላበትን ሰው እስጢፋኖስን ፊልጶስንም ጵሮኮሮስንም ኒቃሮናንም ጢሞናንም ጳርሜናንም ወደ ይሁዲነት ገብቶ የነበረውን የአንጾኪያውን ኒቆላዎስንም መረጡ። ፮በሐዋርያትም ፊት አቆሙአቸው፥ ከጸለዩም በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው። ፯የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፥ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቍጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ። ፰እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር። ፱የነፃ ወጪዎች ከተባለችው ምኵራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያም ሰዎች ከኪልቅያና ከእስያም ከነበሩት አንዳንዶቹ ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር፤ ፲ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም። ፲፩በዚያን ጊዜ። በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሡ። ፲፪ሕዝቡንና ሽማግሌዎችንም ጻፎችንም አናደዱ፥ ቀርበውም ያዙት ወደ ሸንጎም አመጡትና። ፲፫ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰው ስፍራ በሕግም ላይ የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም፤ ፲፬ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ ያፈርሰዋል ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዓት ይለውጣል ሲል ሰምተነዋልና የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አቆሙ። ፲፭በሸንጎም የተቀመጡት ሁሉ ትኵር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት።