፩ወደ ደርቤንና ወደ ልስጥራንም ደረሰ። እነሆም፥ በዚያ የአንዲት ያመነች አይሁዳዊት ልጅ ጢሞቴዎስ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ፤ አባቱ ግን የግሪክ ሰው ነበረ። ፪ለእርሱም በልስጥራንና በኢቆንዮን ያሉ ወንድሞች መሰከሩለት። ፫ጳውሎስ ይህ ከእርሱ ጋር ይወጣ ዘንድ ወደደ፥ በእነዚያም ስፍራዎች ስለ ነበሩ አይሁድ ይዞ ገረዘው፤ አባቱ የግሪክ ሰው እንደ ሆነ ሁሉ ያውቁ ነበርና። ፬በከተማዎችም ሲዞሩ በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የቈረጡትን ሥርዓት ይጠብቁ ዘንድ ሰጡአቸው። ፭አብያተ ክርስቲያናትም በሃያማኖት ይበረቱ ነበር፥ በቍጥርም ዕለት ዕለት ይበዙ ነበር። ፮በእስያም ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አገር አለፉ፤ ፯በሚስያም አንጻር በደረሱ ጊዜ ወደ ቢታንያ ይሄዱ ዘድን ሞከሩ፥ የኢየሱስ መንፈስም አልፈቀደላቸውም፤ ፰በሚስያም አጠገብ አልፈው ወደ ጢሮአዳ ወረዱ። ፱ራእይም ለጳውሎስ በሌሊት ታየው፤ አንድ የመቄዶንያ ሰው። ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን እያለ ቆሞ ሲለምነው ነበር። ፲ራእዩንም ካየ በኋላ ወዲያው ወደ መቄዶንያ ልንወጣ ፈለግን፥ ወንጌልን እንሰብክላቸው ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ጠራን መስሎናልና። ፲፩ከጢሮአዳም ተነሥተን በቀጥታ ወደ ሳሞትራቄ በነገውም ወደ ናጱሌ በመርከብ ሄድን፤ ፲፪ከዚያም ወደ ፊልጵስዩስ ደረስን፤ እርስዋም የመቄዶንያ ከተማ ሆና የወረዳ ዋና ከተማና ቅኝ አገር ናት፤ በዚህችም ከተማ አንዳንድ ቀን እንቀመጥ ነበር። ፲፫በሰንበት ቀንም ከከተማው በር ውጭ የጸሎት ስፍራ በዚያ መሆኑን ስላሰብን ወደ ወንዝ አጠገብ ወጣን፤ ተቀምጠንም ለተሰበሰቡት ሴቶች ተናገርን። ፲፬ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት። ፲፭እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ። በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፥ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ ብላ ለመነችን፤ በግድም አለችን። ፲፮ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን። ፲፯እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች። የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኽ ነበር። ፲፰ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን። ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ። ፲፱ጌቶችዋም የትርፋቸው ተስፋ እንደ ወጣ ባዩ ጊዜ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው ወደ ገበያ በሹማምት ፊት ጐተቱአቸው፤ ፳ወደ ገዢዎችም አቅርበው። እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ከተማችንን እጅግ ያናውጣሉ። ፳፩እኛም የሮሜ ሰዎች ሆነን እንቀበላቸውና እናደርጋቸው ዘንድ ያልተፈቀደልንን ልማዶች ይናገራሉ አሉ። ፳፪ሕዝቡም አብረው ተነሡባቸው፥ ገዢዎቹም ልብሳቸውን ገፈው በበትር ይመቱአቸው ዘንድ አዘዙ፤ ፳፫በብዙም ከደበደቡአቸው በኋላ ወደ ወኅኒ ጣሉአቸው፥ የወኅኒውንም ጠባቂ ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት። ፳፬እርሱም የዚህን ዓይነት ትእዛዝ ተቀብሎ ወደ ውስጠኛው ወኅኒ ጣላቸው፥ እግራቸውንም በግንድ አጣብቆ ጠረቃቸው። ፳፭በመንፈቀ ሌሊት ግን ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፥ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር ፳፮ድንገትም የወኅኒው መሠረት እስኪናወጥ ድረስ ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ ሆነ፤ በዚያን ጊዜም ደጆቹ ሁሉ ተከፈቱ የሁሉም እስራት ተፈታ። ፳፯የወኅኒውም ጠባቂ ከእንቅልፉ ነቅቶ የወኅኒው ደጆች ተከፍተው ባየ ጊዜ፥ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ይገድል ዘንድ አስቦ ሰይፉን መዘዘ። ፳፰ጳውሎስ ግን በታላቅ ድምፅ። ሁላችን ከዚህ አለንና በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ ብሎ ጮኸ። ፳፱መብራትም ለምኖ ወደ ውስጥ ሮጠ፥ እየተንቀጠቀጠም ከጳውሎስና ከሲላስ ፊት ተደፋ፤ ፴ወደ ውጭም አውጥቶ። ጌቶች ሆይ፥ እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል? ኣላቸው። ፴፩እነርሱም። በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመን አንተና ቤተ ሰዎችህ ትድናላችሁ አሉት። ፴፪ለእርሱና በቤቱም ላሉት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ተናገሩአቸው። ፴፫በሌሊትም በዚያች ሰዓት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፥ ያን ጊዜውንም እርሱ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ፤ ፴፬ወደ ቤቱም አውጥቶ ማዕድ አቀረበላቸው፥ በእግዚአብሔርም ስላመነ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር ሐሤት አደረገ። ፴፭በነጋም ጊዜ ገዢዎቹ። እነዚያን ሰዎች ፍታቸው ብለው ሎሌዎቻቸውን ላኩ። ፴፮የወኅኒውም ጠባቂ። ትፈቱ ዘንድ ገዢዎቹ ልከዋል፤ እንግዲህ አሁን ወጥታችሁ በሰላም ሂዱ ብሎ ይህን ቃል ለጳውሎስ ነገረው። ፴፯ጳውሎስ ግን። እኛ የሮሜ ሰዎች ስንሆን ያለ ፍርድ በሕዝብ ፊት ደብድበው በወኅኒ ጣሉን፤ አሁንም በስውር ይጥሉናልን? አይሆንም ራሳቸው ግን መጥተው ያውጡን አላቸው። ፴፰ሎሌዎቹም ይህን ነገር ለገዢዎች ነገሩ። የሮሜ ሰዎችም እንደ ሆኑ በሰሙ ጊዜ ፈሩ፤ ፴፱መጥተውም ማለዱአቸው፥ አውጥተውም ከከተማ ይወጡ ዘንድ ለመኑአቸው። ፵ከወኅኒውም ወጥተው ወደ ልድያ ቤት ገቡ፥ ወንድሞችንም ባዩ ጊዜ አጽናኑአቸውና ሄዱ።