፩ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናት ሄደ፥ ፪በዚህ መንገድ ያሉትንም ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም ቢያገኝ፥ እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵራቦች ደብዳቤ ከእርሱ ለመነ። ፫ሲሄድም ወደ ደማስቆ በቀረበ ጊዜ ድንገት በእርሱ ዙሪያ ከሰማይ ብርሃን አንጸባረቀ፤ ፬በምድርም ላይ ወድቆ ሳለ። ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የሚለውን ድምፅ ሰማ። ፭ጌታ ሆይ፥ ማን ነህ? አለው። እርሱም። አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል አለው። ፮እየተንቀጠቀጠና እየተደነቀ። ጌታ ሆይ፥ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ? አለው። ጌታም። ተነሥተህ ወደ ከተማ ግባና ታደርገው ዘንድ የሚያስፈልግህን ይነግሩሃል አለው። ፯ከእርሱም ጋር በመንገድ የሄዱ ሰዎች ድምፁን እየሰሙ ማንን ግን ሳያዩ እንደ ዲዳዎች ቁሙ። ፰ሳውልም ከምድር ተነሣ፥ አይኖቹም በተከፈቱ ጊዜ ምንም አላየም፤ እጁንም ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ አገቡት። ፱ሳያይም ሦስት ቀን ኖረ፤ አልበላምም አልጠጣምም። ፲በደማስቆም ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ፥ ጌታም በራእይ። ሐናንያ ሆይ፥ አለው። እርሱም። ጌታ ሆይ፥ እነሆኝ አለ። ፲፩ጌታም። ተነሥተህ ቅን ወደ ሚባለው መንገድ ሂድ፥ በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚሉትን አንድ የጠርሴስ ሰው ፈልግ፤ ፲፪እነሆ፥ እርሱ ይጸልያልና፤ ሐናንያ የሚሉትም ሰው ገብቶ ደግሞ እንዲያይ እጁን ሲጭንበት አይቶአል አለው። ፲፫ሐናንያም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም በቅዱሳንህ ላይ ስንት ክፉ እንዳደረገ ስለዚህ ሰው ከብዙዎች ሰምቼአለሁ፤ ፲፬በዚህም ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን አለው አለ። ፲፭ጌታም። ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ ፲፮ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና አለው። ፲፯ሐናንያም ሄዶ ወደ ቤቱ ገባ፥ እጁንም ጭኖበት። ወንድሜ ሳውል ሆይ፥ ጌታ፥ እርሱም በመጣህበት መንገድ የታየህ ኢየሱስ ነው፥ ደግሞ ታይ ዘንድና መንፈስ ቅዱስ ይሞላብህ ዘንድ ላከኝ አለ። ፲፰ወዲያውም እንደ ቅርፊት ያለ ከዓይኑ ወደቀ፥ ያን ጊዜም ደግሞ አየ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፥ ፲፱መብልም በልቶ በረታ። በደማስቆም ካሉት ደቀ መዛሙርት ጋር ጥቂት ቀን ኖረ። ፳ወዲያውም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በምኵራቦቹ ሰበከ። ፳፩የሰሙትም ሁሉ ተገረሙና። ይህ በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ያጠፋ አይደለምን? ስለዚህስ ታስረው ወደ ካህናት አለቆች ይወስዳቸው ዘንድ ወደዚህ አልመጣምን? አሉ። ፳፪ሳውል ግን እየበረታ ሄደ፥ በደማስቆም ለተቀመጡት አይሁድ ይህ ክርስቶስ እንደ ሆነ አስረድቶ መልስ ያሳጣቸው ነበር። ፳፫ብዙ ቀንም ሲሞላ አይሁድ ሊገድሉት ተማከሩ፤ ፳፬ሳውል ግን አሳባቸውን አወቀ። ይገድሉትም ዘንድ በሌሊትና በቀን የከተማይቱን በር ሁሉ ይጠቀብቁ ነበር፤ ፳፭ደቀ መዛሙርት ግን በሌሊት ወስደው በቅጥር ላይ አሳልፈው በቅርጫት አወረዱት። ፳፮ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርት ጋር ይተባበር ዘንድ ሞከረ፤ ሁሉም ደቀ መዝሙር እንደ ሆነ ስላላመኑ ፈሩት። ፳፯በርናባስ ግን ወስዶ ወደ ሐዋርያት አገባውና ጌታን በመንገድ እንዴት እንዳየውና እንደ ተናገረው በደማስቆም በኢየሱስ ስም ደፍሮ እንዴት እንደ ነገረ ተረከላቸው። ፳፰በጌታም በኢየሱስ ስም ደፍሮ እየተናገረ በኢየሩሳሌም ሲወጣና ሲገባ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ ፳፱ከግሪክ አገርም መጥተው ከነበሩት አይሁድ ጋር ይነጋገርና ይከራከር ነበር፤ እነርሱ ግን ሊገድሉት ፈለጉ። ፴ወንድሞችም ይህን ባወቁ ጊዜ ወደ ቂሣርያ ወሰዱት ወደ ጠርሴስም ሰደዱት። ፴፩በይሁዳም ሁሉና በገሊላ በሰማርያም የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት በሰላም ኖሩ ታነጹም፤ በእግዚአብሔርም ፍርሃትና በመንፈስ ቅዱስ መጽናናት እየሄዱ ይበዙ ነበር። ፴፪ጴጥሮስም በየስፍራው ሁሉ ሲዞር በልዳ ወደሚኖሩ ቅዱሳን ደግሞ ወረደ። ፴፫በዚያም ከስምንት ዓመት ጀምሮ በአልጋ ላይ ተኝቶ የነበረውን ኤንያ የሚሉትን አንድ ሰው አገኘ፤ እርሱም ሽባ ነበረ። ፴፬ጴጥሮስም። ኤንያ ሆይ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስሃል፤ ተነሣ ለራስህም አንጥፍ አለው። ፴፭ወዲያውም ተነሣ። በልዳና በሰሮናም የሚኖሩ ሁሉ እርሱን አይተው ወደ ጌታ ዘወር አሉ። ፴፮በኢዮጴም ጣቢታ የሚሉአት አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፥ ትርጓሜውም ዶርቃ ማለት ነው፤ እርስዋም መልካም ነገር የሞላባት ምጽዋትም የምታደርግ ነበረች። ፴፯በዚያም ወራት ታመመችና ሞተች፤ አጥበውም በሰገነት አኖሩአት። ፴፰ልዳም ለኢዮጴ ቅርብ ናትና ደቀ መዛሙርት ጴጥሮስ በዚያ እንዳለ ሰምተው፥ ወደ እነርሱ ከመምጣት እንዳይዘገይ እየለመኑ ሁለት ሰዎች ወደ እርሱ ላኩ። ፴፱ጴጥሮስም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር መጣ፤ በደረሰም ጊዜ በሰገነት አወጡት መበለቶችም ሁሉ እያለቀሱ ዶርቃ ከእነርሱ ጋር ሳለች ያደረገቻቸውን ቀሚሶችንና ልብሶችን ሁሉ እያሳዩት በፊቱ ቆሙ። ፵ጴጥሮስም ሁሉን ወደ ውጭ አስወጥቶ ተንበርክኮም ጸለየ፥ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ። ጣቢታ ሆይ፥ ተነሺ አላት። እርስዋም ዓይኖችዋን ከፈተች ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ተቀመጠች። ፵፩እጁንም ለእርስዋ ሰጥቶ አስነሣት፤ ቅዱሳንንና መበለቶችንም ጠራ ሕያውም ሆና በፊታቸው አቆማት። ፵፪ይህም በኢዮጴ ሁሉ የታወቀ ሆነ፥ ብዙ ሰዎችም በጌታ አመኑ። ፵፫በኢዮጴም ስምዖን ከሚሉት ከአንድ ቍርበት ፋቂ ጋር አያሌ ቀን ኖረ።