፩በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖንም፥ የቀሬናው ሉክዮስም፥ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስም ባለምዋል ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። ፪እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ። በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ። ፫በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው። ፬እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ። ፭በስልማናም በነበሩ ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ አገልጋይም ዮሐንስ ነበራቸው። ፮ደሴቲቱንም ሁሉ እስከ ጳፉ በዞሩ ጊዜ፥ በርያሱስ የሚሉትን ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ የሆነውን አንድ አይሁዳዊ ሰው አገኙ፤ ፯እርሱም አስተዋይ ሰው ከሆነው ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አገረ ገዥ ጋር ነበረ። ይህም በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ፈለገ። ፰ጠንቋዩ ግን ኤልማስ፥ ስሙ እንዲሁ ይተረጐማልና፥ አገረ ገዡን ከማመን ሊያጣምም ፈልጎ ተቃወማቸው። ፱ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ትኵር ብሎ ሲመለከተው። ፲አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? ፲፩አሁንም፥ እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፥ ዕውርም ትሆናለህ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም አለው። ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፥ በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ። ፲፪በዚያን ጊዜ አገረ ገዡ የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ። ፲፫ጳውሎስም ከጓደኞቹ ጋር ከጳፉ ተነሥቶ የጵንፍልያ ወደምትሆን ወደ ጴርጌን መጣ፤ ዮሐንስም ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። ፲፬እነርሱ ግን ከጴርጌን አልፈው የጲስድያ ወደምትሆን ወደ አንጾኪያ ደረሱ፤ በሰንበትም ቀን ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ። ፲፭ሕግና ነቢያትም ከተነበቡ በኋላ የምኵራቡ አለቆች። ወንድሞች ሆይ፥ ሕዝብን የሚመክር ቃል እንዳላችሁ ተናገሩ ብለው ላኩባቸው። ፲፮ጳውሎስም ተነሣና በእጁ ጠቅሶ እንዲህ አለ። የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ፥ ስሙ። ፲፯የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መርጦ በግብፅ አገር በእንግድነት ሳሉ ሕዝቡን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፥ ከፍ ባለችውም ክንዱ ከዚያ አወጣቸው። ፲፰በበረሀም አርባ ዓመት ያህል መገባቸው። ፲፱በከነዓንም አገር ሰባት አሕዛብን አጥፍቶ ምድራቸውን አወረሳቸው። ፳ከዚህም በኋላ እስከ ነቢዩ እስከ ሳሙኤል ድረስ አራት መቶ አምሳ ዓመት ያህል መሳፍንትን ሰጣቸው። ፳፩ከዚያም ወዲያ ንጉሥን ያነግሥላቸው ዘንድ ለመኑ፥ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሚሆን ሰው የቂስን ልጅ ሳኦልን አርባ ዓመት ሰጣቸው፤ ፳፪እርሱንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን በእነርሱ ላይ እንዲነግሥ አስነሣው፥ ሲመሰክርለትም። እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ አለ። ፳፫ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል ለእስራኤል መድኃኒትን እርሱም ኢየሱስን አመጣ። ፳፬ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር። ፳፭ዮሐንስም ሩጫውን ሲፈጽም ሳለ። እኔ ማን እንደ ሆንሁ ታስባላችሁ? እኔስ እርሱን አይደለሁም፤ ነገር ግን እነሆ፥ የእግሩን ጫማ እፈታ ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል ይል ነበር። ፳፮እናንተ ወንድሞቻችን፥ የአብርሃም ዘር ልጆች ከእናንተ መካከልም እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፥ ለእናንተ የዚህ የመዳን ቃል ተላከ። ፳፯በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው እርሱንና በየሰንበቱ የሚነበቡትን የነቢያትን ድምፆች ስላላወቁ በፍርዳቸው ፈጽመዋልና፤ ፳፰ለሞትም የሚያደርስ ምክንያት አንድ ስንኳ ባያገኙበት፥ ይገድለው ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት፤ ፳፱ስለ እርሱም የተጻፈውን ሁሉ በፈጸሙ ጊዜ ከእንጨት አውርደው በመቃብር አኖሩት። ፴እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤ ፴፩በሕዝብም ዘንድ ምስክሮቹ ለሆኑት ከእርሱ ጋር ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ለወጡት ብዙ ቀን ታያቸው። ፴፪እኛም ለአባቶች የተሰጠውን ተስፋ የምስራቹን ለእናንተ እንሰብካለን፤ ፴፫ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ። አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአልና። ፴፬እንደገናም ወደ መበስበስ እንዳይመለስ ከሙታን እንደ አስነሣው፥ እንዲህ። የታመነውን የዳዊትን ቅዱስ ተስፋ እሰጣችኋለሁ ብሎአል። ፴፭ደግሞ በሌላ ስፍራ። ቅዱስህን መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም ይላልና። ፴፮ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፥ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤ ፴፯ይህ እግዚአብሔር ያስነሣው ግን መበስበስን አላየም። ፴፰-፵፪በወጡም ጊዜ ይህን ነገር በሚመጣው ሰንበት ይነግሩአቸው ዘንድ ለመኑአቸው። ፵፫ጉባኤውም ከተፈታ በኋላ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ገብተው ከሚያመልኩ ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፥ እነርሱም ሲነግሩአቸው በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አስረዱአቸው። ፵፬በሁለተኛውም ሰንበት ከጥቂቶቹ በቀር የከተማው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ። ፵፭አይሁድም ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ ቅንዓት ሞላባቸው፥ እየተሳደቡም ጳውሎስ የተናገረውን ቃል ተቃወሙ። ፵፮ጳውሎስና በርናባስም ገልጠው። የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፥ እነሆ፥ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን። ፵፯እንዲሁ ጌታ። እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ ብሎ አዞናልና አሉ። ፵፰አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፥ ለዘላለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ፤ ፵፱የጌታም ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ። ፶አይሁድ ግን የሚያመልኩትን የከበሩትንም ሴቶችና የከተማውን መኳንንት አወኩ፥ በጳውሎስና በበርናባስም ላይ ስደትን አስነሥተው ከአገራቸው አወጡአቸው። ፶፩እነርሱ ግን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈውባቸው ወደ ኢቆንዮን መጡ። ፶፪በደቀ መዛሙርትም ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው።