፩ወደ ኢጣሊያም በመርከብ እንሄድ ዘንድ በተቈረጠ ጊዜ፥ ጳውሎስንና ሌሎችን እስረኞች ከአውግስጦስ ጭፍራ ለነበረ ዩልዮስ ለሚሉት ለመቶ አለቃ አሳልፈው ሰጡአቸው። ፪በእስያም ዳርቻ ወዳሉ ስፍራዎች ይሄድ ዘንድ ባለው በአድራሚጢስ መርከብ ገብተን ተነሣን፤ የመቄዶንያም ሰው የሆነ የተሰሎንቄው አርስጥሮኮስ ከእኛ ጋር ነበረ። ፫በነገውም ወደ ሲዶና ስንደርስ ዩልዮስ ለጳውሎስ ቸርነት አድርጎ እርዳታቸውን ይቀበል ዘንድ ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድ ፈቀደለት። ፬ከዚያም ተነሥተን ነፋሱ ፊት ለፊት ነበረና በቆጵሮስ ተተግነን ሄድን፤ ፭በኪልቅያና በጵንፍልያም አጠገብ ያለውን ባሕር ከተሻገርን በኋላ በሉቅያ ወዳለ ወደ ሙራ ደረስን። ፮የመቶ አለቃውም በዚያ ወደ ኢጣሊያ የሚሄድ የእስክንድርያውን መርከብ አግኝቶ ወደ እርሱ አገባን። ፯ብዙ ቀንም እያዘገምን ሄደን በጭንቅ ወደ ቀኒዶስ አንጻር ደረስን፤ ነፋስም ስለ ከለከለን በቀርጤስ ተተግነን በሰልሙና አንጻር ሄድን፤ ፰በጭንቅም ጥግ ጥጉን አልፈን ለላሲያ ከተማ ወደ ቀረበች መልካም ወደብ ወደሚሉአት ስፍራ መጣን። ፱ብዙ ጊዜም ካለፈ በኋላ፥ የጦም ወራት አሁን አልፎ ስለ ነበረ በመርከብ ለመሄድ አሁን የሚያስፈራ ነበርና ጳውሎስ። ፲እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ይህ ጕዞ በጥፋትና በብዙ ጕዳት እንዲሆን አያለሁ፤ ጥፋቱም በገዛ ሕይወታችን ነው እንጂ በጭነቱና በመርከቡ ብቻ አይደለም ብሎ መከራቸው። ፲፩የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስ ከተናገረው ይልቅ የመርከብ መሪውንና የመርከቡን ባለቤት ያምን ነበር። ፲፪ያም ወደብ ይከርሙበት ዘንድ የማይመች ስለ ሆነ፥ የሚበዙቱ ቢቻላቸው በሰሜንና በደቡብ ምዕራብ ትይዩ ወዳለው ፍንቄ ወደሚሉት ወደ ቀርጤስ ወደብ ደርሰው ይከርሙ ዘንድ ከዚያ እንዲነሡ መከሩ። ፲፫ልከኛም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ፥ እንዳሰቡት የሆነላቸው መስሎአቸው ተነሡ በቀርጤስም አጠገብ ጥግ ጥጉን አለፉ። ፲፬ነገር ግን እጅግ ሳይዘገይ አውራቂስ የሚሉት ዓውሎ ነፋስ ከዚያ ወረደባቸው፤ ፲፭መርከቡም ተነጥቆ ነፋሱን ሲቃወም መሄድ ስላልቻለ ለቀነው ተነዳን። ፲፮ቄዳ በሚሉአትም ደሴት በተተገንን ጊዜ ታንኳይቱን ለመግዛት በጭንቅ ቻልን፤ ፲፯ወደ ላይም ካወጡአት በኋላ መርከቡን በገመድ አስታጥቀው አጸኑ፤ ስርቲስም ወደሚሉት ወደ አሸዋ እንዳይወድቁ ፈርተው ሸራውን አውርደው እንዲሁ ተነዱ። ፲፰ነፋሱም በርትቶ ሲያስጨንቀን በማንግሥቱ ከጭነቱ ወደ ባሕር ይጥሉ ነበር፥ ፲፱በሦስተኛውም ቀን የመርከቡን ዕቃ በእጃችን ወረወርን። ፳ብዙ ቀንም ፀሐይን ከዋክብትንም ሳናይ ትልቅ ነፋስም ሲበረታብን ጊዜ፥ ወደ ፊት እንድናለን የማለት ተስፋ ሁሉ ተቈረጠ። ፳፩ሳይበሉም ብዙ ቀን ከቆዩ በኋላ፥ ያን ጊዜ ጳውሎስ በመካከላቸው ቆሞ እንዲህ አለ። እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ሰምታችሁኝ በሆነ ኖሮ ከቀርጤስ እንዳትነሡ ይህንም ጥፋትና ጕዳት እንዳታገኙ ይገባችሁ ነበር። ፳፪አሁንም። አይዞአችሁ ብዬ እመክራችኋለሁ፤ ይህ መርከብ እንጂ ከእናንተ አንድ ነፍስ እንኳ አይጠፋምና። ፳፫የእርሱ የምሆንና ደግሞ የማመልከው የእግዚአብሔር መልአክ በዚች ሌሊት በአጠገቤ ቆሞ ነበርና፥ እርሱም። ፳፬ጳውሎስ ሆይ፥ አትፍራ፤ በቄሣር ፊት ልትቆም ይገባሃል፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር የሚሄዱትን ሁሉ ሰጥቶሃል አለኝ። ፳፭ስለዚህ እናንተ ሰዎች ሆይ፥ አይዞአችሁ፤ እንደ ተናገረኝ እንዲሁ እንዲሆን እግዚአብሔርን አምናለሁና። ፳፮ነገር ግን ወደ አንዲት ደሴት እንድንወድቅ ያስፈልገናል። ፳፯በአሥራ አራተኛውም ሌሊት በአድርያ ባሕር ወዲህና ወዲያ ስንነዳ፥ መርከበኞች በእኩለ ሌሊት ወደ አንድ ምድር የቀረቡ መሰላቸው። ፳፰መለኪያ ገመድም ቢጥሉ ሀያ በሰው ቁመት አገኙ ጥቂትም ቆይተው ሁለተኛ ቢጥሉ አሥራ አምስት በሰው ቁመት አገኙ፤ ፳፱ድንጋያማም ወደ ሆነ ስፍራ እንዳይወድቁ ፈርተው፥ ከመርከቡ በስተኋላ አራት መልሕቅ አወረዱ፥ ቀንም እንዲሆን ተመኙ። ፴መርከበኞቹም ከመርከቡ ይሸሹ ዘንድ ፈልገው ከመርከቡ በስተ ፊት መልሕቅ መጣል እንዳላቸው አመካኝተው ታንኳይቱን ወደ ባሕር ባወረዱ ጊዜ፥ ፴፩ጳውሎስ ለመቶ አለቃውና ለወታደሮቹ። እነዚህ በመርከቡ ካልቆዩ እናንተ ትድኑ ዘንድ አትችሉም አላቸው። ፴፪ያን ጊዜ ወታደሮቹ የታንኳይቱን ገመድ ቈርጠው ትወድቅ ዘንድ ተዉአት። ፴፫ቀንም ሲነጋ ጳውሎስ ምግብ ይበሉ ዘንድ ሁሉን ይለምን ነበር፥ እንዲህም አላቸው። እየጠበቃችሁ ምንም ሳትቀበሉ ጦማችሁን ከሰነበታችሁ ዛሬ አሥራ አራተኛ ቀናችሁ ነው። ፴፬ሰለዚህ ምግብ ትበሉ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ ይህ ለደኅንነታችሁ ይሆናልና፤ ከእናንተ ከአንዱ የራስ ጠጕር እንኳ አትጠፋምና። ፴፭ይህንም ብሎ እንጀራን ይዞ በሁሉ ፊት እግዚአብሔርን አመሰገነ ቈርሶም ይበላ ዘንድ ጀመረ። ፴፮ሁለም ተጽናንተው ራሳቸው ደግሞ ምግብ ተቀበሉ። ፴፯በመርከቡም ያለን ሁላችን ሁለት መቶ ሰባ ስድስት ነፍስ ነበርን። ፴፰በልተውም በጠገቡ ጊዜ ስንዴውን ወደ ባሕር እየጣሉ መርከቡን አቃለሉት። ፴፱በነጋም ጊዜ ምድሩን አላወቁትም፥ ነገር ግን የአሸዋ ዳር ያለውን የባሕር ስርጥ ተመለከቱ፥ ቢቻላቸውም መርከቡን ወደዚያ ይገፉ ዘንድ ቈረጡ። ፵መልሕቆቹንም ፈትተው በባሕር ተዉአቸው፥ ያን ጊዜም የመቅዘፊያውን ማሠሪያ ፈቱት፤ ታናሹንም ሸራ ለነፋስ ከፍ አድርገው ወደ ዳር አቅንተው ይሄዱ ዘንድ ጀመሩ። ፵፩ነገር ግን ሁለት ባሕር በተገናኙበት ስፍራ ወድቀው መርከቡን በዲብ ላይ ነዱ፤ በስተ ፊቱም ተተክሎ የማይነቃነቅ ሆነ፥ በስተ ኋላው ግን ከማዕበሉ ግፊያ የተነሣ ይሰበር ነበር። ፵፪ወታደሮቹም ከእስረኞች አንድ ስንኳ ዋኝቶ እንዳያመልጥ ይገድሉአቸው ዘንድ ተማከሩ። ፵፫የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስን ያድነው ዘንድ አስቦ ምክራቸውን ከለከለ፤ ዋና የሚያውቁትም ከመርከብ ራሳቸውን እየወረወሩ አስቀድመው ወደ ምድር ይወጡ ዘንድ፥ ፵፬የቀሩትም እኵሌቶቹ በሳንቃዎች ላይ እኵሌቶቹም በመርከቡ ስባሪ ይወጡ ዘንድ አዘዘ። እንዲሁም ሁሉ በደኅና ወደ ምድር ደረሱ።